7ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ በወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው

123

ሰኔ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ያዘጋጀው 7ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው።

አውደ ርዕዩ “የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የብልጽግና ጉዛችንን በሳይንስና ፈጠራ ዕውን እናደርጋለን!” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው፡፡

የሳይንስና የፈጠራ ስራ አውደ ርዕዩ በዋናነት በሳይንስ ፈጠራ የዳበረ ትውልድ መፍጠርን መሰረት አድርጎ የሚካሄድ ነው።

መርሀ-ግብሩም በተማሪዎች መካከል ጤናማ ውድድርን በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ተገልጿል።

በተለይም በንድፍ ሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ለመቀየርና የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎች የሚበረታቱበት አሰራር በትምህርት ቤቶች እየተተገበሩ መሆኑ የሚታይበት ነው ተብሏል።

በአውደ ርዕዩ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች እንደየ ክፍል ደረጃቸው በተለያዩ ዘርፎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተጠቁሟል።

በአውደ ርዕዩ ላይ የተሻለ የፈጠራ ስራ ለሚያቀርቡ ተማሪዎችና መምህራን እውቅና እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

በአውደ ርዕዩ በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች፤በአይ ሲቲ፤በልዩ ፍላጎት እንዲሁም በስነ ጥበብ ዘርፎች በተማሪዎችና በመምህራን የተዘጋጁ የፈጠራ ስራዎች ቀርበዋል።

በአውደ ርዕዩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው፣የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፣የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቢሮ አመራሮች እና ስራተኞች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም