በቅዱስ ያሬድ ስም ግዙፍ የምርምር ማዕከልና ሙዚየም ሊገነባ ነው

185

ሰኔ 8/2014/ኢዜአ/ በቅዱስ ያሬድ ስም ግዙፍ የምርምር ማዕከል፣ ሙዚየም፣ ቤተመጻህፍትና ሌሎችንም ያካተተ የ3 ቢሊየን ብር የግንባታ ፕሮጀክት ሊጀመር ነው።

የደብረ ሐዊ  ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም አሰሪ ኮሚቴ የምርምር ማዕከሉንና የሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ  ለመገናኛ  ብዙሃን  መግለጫ  ሰጥቷል።

የኮሚቴው ምክትል ስራ አስፈፃሚ አርክቴክት ተስፋ ማርያም ተሾመ፤ ፕሮጀክቱ በ6 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍ ገልፀዋል።

የግንባታ ቦታውም ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በየዳ ወረዳ ሲሆን መሬቱም ከአካባቢው ማኅበረሰብ የተበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉና ሙዚየሙ የሚገነባበት ሥፍራ የራስ ዳሽን ተራራና የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ በመሆኑ ለቱሪስት መስህብነት እንዲውል ያስችለዋልም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በውስጡ የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም፣ የምርምር ማዕከል፣ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ሙዚየም፣ ቤተመጻሕፍት ዓመታዊ ሀገራዊ የማህሌት ትዕይንት የሚቀርብበት መድረክን እንደሚያካትት  ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በ3 ቢሊየን ብር የሚገነባ ሲሆን ከተለያዩ አካላት በሚሰበሰብ ገንዘብ እንደሚሰራ ተገልጿል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም በመጪው ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጠቁመው ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ5 እስከ 7 ዓመታት ሊፈጅ አንደሚችል አርክቴክት ተስፋማርያም ተሾመ ጠቁመዋል።

ቅዱስ ያሬድ ሚያዚያ 5 ቀን 505 ዓ.ም በአክሱም ከተማ የተወለደ ሲሆን የዜማ ፈጣሪ፣ ባለቅኔ ከመሆኑምባሻገር የሥነ-ትርጓሜ እውቀቱ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።

ስለያሬዳዊ ዝማሬ ሲነሳ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዕለት ተዕለት መንፈሳዊ አገልግሎት ቅዱስ ያሬድ ያበረከታቸው የግዕዝ፣ ዕዝልና አራራይ ዜማዎች በየዕለቱ በቅዳሴ፣ በማኅሌትና ሰዓታቱ ምልኮታዊ ሥነ-ስርዓቱን የሚያደምቁ እንደሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም