የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ስራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው

107

ሰኔ 08 2014(ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ስራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ሴቶች በፈጠራው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር ሹመይ በርሄ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ባዋቀረው የቢዝነስ ማዕከል የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ የፈጠራ ስራዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ለአብነትም የጎዳና ላይ ንግድን በዘመናዊ እና ተንቀሳቃሽ መሸጫ ሱቆች ለመተካት ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

በስምምነቱ መሰረት በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች ተንቀሳቃሽ መሸጫ ሱቅ መሰራቱን ተናግረው ተንቀሳቃሽ ሱቁ ምግቦችን፣ መጻህፍት እና አልባሳትን ጨምሮ አነስተኛ ምርቶችን ለመሸጥ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

May be an image of monument and outdoors

በዩንቨርሲቲው የተሰራውን የተንቀሳቃሽ መሸጫ ሱቅ ቴክኖሎጂን ወደ ገበያ ለማውጣት በተደረገ ውድድር ዩኒቨርስቲው 500 ሺህ ብር ማሸነፉንም ተናግረዋል።

የሽመና ሥራን የሚያቀልና ራሱን በራሱ የሚያሽከረክር /አውቶማቲክ/ የክር ማጠንጠኛ ወደ ገበያ ለማውጣት ዩኒቨርስቲው በዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ሴቶችን በፈጠራ ዘርፍ ለማሳተፍና ለማበረታታት እየሰራ ስለመሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በአምስት ዘርፎች የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ሴቶች እያወዳደረ መሆኑን ጠቁመው የፈጠራ ሥራዎቹ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ይችላሉ፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ የማህበረሰቡን ችግር ያቃልላሉ የሚለው መስፈርት ከግምት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም