በጋዜጠኝነት ሙያው ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋለ አንድም ግለሰብ የለም-የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን

127

ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በወንጀል የተጠረጠረ እንጂ በጋዜጠኝነት ሙያው ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋለ አንድም ግለሰብ አለመኖሩን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ማብራሪያ በሰጡበት ማብራርያ የጋዜጠኝነት ሙያን የወንጀል መሸፈኛ፤ የሕገ-ወጥ ጥቅም ማካበቻ ማድረግ እንደማይገባ ተናግረው ነበር።

በሀገሪቱ ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በሃይማኖት፣ በብሔርና ሌሎችም ምክንያቶች ለማጋጨት እየሰሩ፤ የሀገር መከታ የሆነውን መከላከያ ሰራዊት እያንቋሸሹ ያሉ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።

በመሆኑም በዚህ ወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚውሉ አክቲቪስቶች በጋዜጠኛ ስም ሽፋን ማድረጋቸው ተቀባይነት የሌለውና ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም  በሕግ ሲጠየቁ "ጋዜጠኛ" በሚል ሽፋን ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት እንደሌለውና ሕግ የሚተላለፉ ሁሉ ተጠያቂ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ፤ እስካሁን በወንጀል የተጠረጠረ እንጂ በጋዜጠኝነቱ በቁጥጥር ስር የዋለ  አንድም ግለሰብ የለም ብለዋል።

ሰሞኑን በሕግ ጥላ ስር ከዋሉት መካከል ከአንድ ግለሰብ በስተቀር ሌሎቹ የጋዜጠኝነት ፍቃድ የሌላቸው መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ፍቃድ ያለው ግለሰብም ቢሆን በቁጥጥር ስር የዋለው የሀገሪቱን ሕግ ተላልፏል በሚል በወንጀል ተጥርጥሮ እንጂ በሙያው አይደለም ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋዜጠኛ ብሎ የሚጠራው በሚዲያ ተቋም ደረጃ የተመዘገበ መስሪያ ቤት የሚሰሩ ሙያተኞችንና በግለሰብ ደረጃ የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቃድ ያወጡትን ነው ሲሉም አስረድተዋል።

በመሆኑም አብዛኞቹ ግለሰቦች ለሆነ የፖለቲካ ቡድን በውግንና የቆሙና በወንጀል ሲፈለጉ ጋዜጠኛ እንደሆኑ የሚያስመስሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ዜጎች ሕጋዊውን ስርዓት ተከትለው በመመዝገብ የሀገሪቱን ሕግና ስርዓት አክብረው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በመደበኛ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ግለሰቦችም ቢሆኑ ሕግና ስርዓትን አክበረው ለሀገሪቱ አንድነትና ሰላም የመስራት ግደታ አለባቸው ያሉት ኃላፊው ይህ ካልሆነ ግን በሕገ መንግስቱና ይህንን መሰረት አድርገው በወጡ ህጎች ተጠያቂ ይሆናሉ ነው ያሉት።

ከምንም በላይ ትክክለኛ ጋዜጠኞች ሙያቸው በሌሎች ሲበላሽ ቆመው መመልከት የለባቸውም  ሲሉ የገለጹት አቶ መሐመድ ህዝብም ቢሆን ሀገርን ከሚጎዳ የጥላቻና የሀሰተኛ መረጃ ራሱን ማራቅ አለበት በማለት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም