በፈጠራ ስራ ለሃገራችን የድርሻችንን ለማበርከት ጥረት እያደረግን ነው - ተማሪዎች

91

አሶሳ (ኢዜአ) ሰኔ 08/2014........ ለሀገር እድገት የድርሻቸውን ለማበርከት የሚያግዙ የፈጠራ ስራዎችን ለማውጣት እንደሚተጉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

በዩኒቨርሲቲው “ፈጠራ ለተሻለ የማህበረሰብ ህይወት” በሚል በተካሄደው የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር ሲምፖዚዬም ከ26 በላይ የፈጠራ ስራዎች ቀርበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ተማሪዎቹ ያቀረቧቸው የፈጠራ ስራዎች የህብረተሰቡን ችግሮች መሰረት አድርገው እንዲሰሩ አቅጣጫ ከማሳየት ጀምሮ ውጤት እንደተገኘባቸው አመልክተዋል፡፡

የፈጠራ ስራዎችን ካቀረቡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ወጣት ፈክረዲን ጀማል ከወዳደቁ እቃዎች ዘመናዊ የማሽላ መፈልፈያ ማሽንና ሌሎች ማሽኖችን መስራቱን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ የፈጠራ ስራዎቹን ሲጀምር ዓላማ ያደረገው በተለይም በዓለም ላይ ግጭት፣ በሽታ እና ሌሎችም ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚከሰተውን የቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እጥረት በራስ ለመተካት እንዲቻል ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በተለይም የሃገር መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ እና የሃገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነውን ግብርናን ለማዘመን የድርሻውን መወጣት እንደሚፈልግም ተናግሯል፡፡

የግብዓትና የቁሳቁስ አቅርቦት ቢኖር በሙከራ ደረጃ የሠራቸውን በተሻለ ጥራት እና ብዛት በማምረት ለኢኮኖሚው የድርሻውን የማበርከት እቅድ እንዳለው ተማሪ ፈክረዲን አመልክቷል፡፡

ወላጆች በዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ልጆቻቸውን የትምህርት ውጤት ጨምሮ የመማር ማስተማሩን ሂደት ቤታቸው ሆነው ሊከታተሉ የሚያስችል የኮምፒዩተር ፕሮግራም ያዘጋጀችው ደግሞ ተማሪ ሄራን ደምስ ናት፡፡

ሀገራችንን በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከወረቀት አሰራር ተላቀን ወደ ኮምፒዩተር ሲስተም መግባት የግድ ይለናል ትላለች፡፡

ሁሉም ተማሪ በንድፈ ሃሳብ የተማረውን ወደ ተግባር በመቀየር ለሃገሩ የድርሻውን ማበርከት እንዳለበትም ገልጻለች፡፡

ህብረተሰቡን በአጭር ጊዜ ከድህነት ለማላቀቅ የሚያግዙ ፈጠራዎችን መስራት እንችላለን የምትለው ወጣት ሄራን በግሏ ሌሎችንም የፈጠራ ስራዎች በማከናወን የድርሻዋን የመወጣት ራዕይ እንዳላት አስታውቃለች፡፡

በጸሃይ ብርሃን ጭምር የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማሽን የሠራው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር መብራቱ ዋለው በበኩሉ ችግር ፈቹ የፈጠራ ስራ በተለይ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ከውጪ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በማስቀረት የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ አቅም እንደሚሳድግም በማከል።

የፈጠራ ስራውን በስፋት ወደ ገበያ በማቅረብ እና ለአርሶ አደሩ በማዳረስ ለድህነት ቅነሳው የድርሻውን የማበርከት ራዕይ እንዳለውም መምህር መብራቱ አስታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ለችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ትኩረት የሰጠው ከ2009 ጀምሮ ነው፡፡

ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያቀረቧቸው የፈጠራ ስራዎች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸው በተለይም የህብረተሰቡ ችግሮች መሰረት አድርገው እንዲሰሩ አቅጣጫ ከማሳየት ጀምሮ ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የፈጠራ ስራዎቹ በቀጣይም ወደ ማህብረሰቡ ወርደው ተግባራዊ እስከሚሆኑ ድረስ ዩኒቨርሲቲው በጀትን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ዶክተር ሃይማኖት አስታውቀዋል፡፡

የተማሪዎቹ የፈጠራ ስራ ከራሳቸው አልፎ ዩኒቨርሲቲውን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ተሸላሚ እያደረጉ መሆናቸውንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም