በዞኑ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ የሰው እገታና ግድያ ወንጀሎች እንዲቀንሱ አስችሏል

108

መተማ፤ ሰኔ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ሥራ ይፈፀሙ የነበሩ የሰው እገታና ግድያ ወንጀሎች መቀነሳቸውን የመተማ ዮሃንስና ገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የመተማ ዮሓንስ ከተማ ነዋሪ አቶ ስጦታው ጫኔ እንዳሉት "በዞኑ ጫካንና ህዝብን ተገን በማድረግ ህገወጦች ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡና ልማትን እንዳይሰሩ በየጊዜው ወንጀል ሲፈፅሙ ቆይተዋል"።

ለዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ በርካታ ፀረ ሰላም ቡድኖች እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን እየተሰራ ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ቡድኖቹ ለህግ እንዲቀርቡ በመደረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

''በተለይ እንደዚህ ዞን የህግ ማስከበር ስራው ዘግይቷል'' ያሉት ነዋሪው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውና የተገኘውን ሰላም የበለጠ አስተማማኝ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

መንግስት እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበር ስራ ለበርካታ ጊዜያት በህብረተሰቡ ዘንድ ሲጠየቅ የቆየ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበር የገለጹት ደግም የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሬም አባይ ናቸው።

''ይህ ዞን በየሳምንቱ አለፍ ሲልም በየቀኑ ሰው ሚታገትበት፣ ሚገደልበትና ሚዘረፍበት አካባቢ ነበር'' ያሉት ነዋሪዋ ከህግ ማስከበሩ እርምጃው ብኋላ ከፍተኛ መሻሻል መኖሩን ተናግረዋል።

"ከመተማ ጎንደርና ከመተማ ቋራ ለመሄድ ከፍተኛ ስጋት ነበረብን " ሲሉ ጠቅሰው መንግስት ተግባሩን በመቀጠል ፀረ ሰላምና ልማት ኃይሎችን ለህግ እንዲያቀርብ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ በበኩላቸው የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የኦፕሬሽንና የህዝብ ግንኙነት እቅድ ተዘጋጅቶ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ በርካታ ቁጥር ያላቸውና በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ አካላት በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ መደረጉን ጠቅሰዋል።

"በአካባቢው ቀደም ሲል ህገ ወጥነት ተበራክቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይ "የሰው እገታ፣ ዝርፊያ፣ የነብስ ግድያና መሰል ወንጀሎች ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ አማረውት ነበር" ብለዋል።

በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ ህግ ይከበር የሚል ጠንካራ ጥያቄ ሲያነሳ እንደነበርና ለጥያቄው መፍትሄ ለመስጠት የህግ ማስክበር ዘመቻ መካሄዱን አስታውቀዋል።

በተወሰደው እርምጃም 100 የሚጠጉ ወንጅለኞችን በህግ ጥላ ስር ማዋል በመቻሉ አሁን ላይ ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል።

የዞኑን ህዝብ የመልማትና በሰላም ወጥቶ የመግባት ሰላማዊ ሁኔታን እውን ለማድረግ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።

የዞኑ ህዝብ አሁን የታየውን ሰላማዊ የፀጥታ ሁኔታ ዘላቂ ለማድረግ መላ ህዝቡ በህግ የበላይነት መረጋገጥ ላይ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም