የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በሁለት ወራት ውስጥ እድሳቱ ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ይሆናል

372

ሰኔ 8/2014/ኢዜአ/ የሀገር ፍቅር ቴአትር በሁለት ወራት ውስጥ ዕድሳቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አብዱልከሪም ጀማል ተናገሩ።

በአፍሪካ አንጋፋው ቴአትር ቤት (የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት) በሀገር ወዳዶች አደራጅነት ሐምሌ 11  ቀን 1927 ዓ.ም ነበር የተመሰረተው።

ኢትዮጵያን ከፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ለመታደግ ጥበብ ያላትን የመቀስቀስ ሚና በመረዳት 'የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማህበር' በሚል ስያሜ የተቋቋመው ቤተ-ጥበብ ከተመሰረተ የፊታችን ሐምሌ 87 ዓመታትን ይደፍናል።

ቴአትር ቤቱ በተውኔት፣ በውዝዋዜና በሙዚቃው ዘርፍ አንቱ የተሰኙ ተዋንያንና ከያኒያንን ያፈራ ሲሆን ኢዩኤል ዮሐንስ፣ ፍሬው ኅይሉ፣ አሰፋ አባተ፣ መላኩ በጎሰው፣ በሻህ ተክለማርያም፣ አብራር አብዶ፣ አስቴር አወቀ፤ ጥላሁን ገሠሠ፣ ንጋቷ ከልካይና አሰለፈች አሸኔ ይጠቀሳሉ።

በኮቪድ 19 ዋዜማ ጀምሮ በዕደሳት ላይ የቆየው ቴአትር ቤቱ አሁን ላይ የእድሳት ስራ እየተጠናቀቀ ሲሆን፤ የወንበር መግጠም፣ መጋረጃ እና መሰል የፊኒሺንግ ስራዎችን የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም ጀማል ለኢዜአ ገልጸዋል።

ቀሪ ስራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ቢበዛ እስከ ሁለት ወራት ባሉት ጊዜያት ቴአትር ቤቱ ለስራ ዝግጁ ሆኖ ክፍት ይሆናል ብለዋል።

ዕድሳቱ የቀደመ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ አግባብ መከወኑና የዕደሳት ሂደቱም በከተማው ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ክትትል እንደተፈጸመ ገልጸዋል።

ቴአትር ቤቱ ለህዝብ ክፍት ሲደረግም ቀደም ሲል ለተመልካች ዕይታ ቀርበው ከተቋረጡ ሁለት ተውኔቶች በተጨማሪ አራት አዳዲስ ተውኔቶች ለመድረክ ዕይታ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዕድሳት መከናወኑ ለቴአትር ደንበኞችና ለመድረክ ከያኒያን ምቾት ስለሚፈጥር ቴአትር ቤቱ የተሻለ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ለማቅረብ እና ደንበኞችን ለመሳብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት 128 ቋሚ ሰራተኞች የሚያስተዳድር ሲሆን ስራ አቁሞ በቆየበት ላለፉት 19 ወራት ገደማ ዕድሳት ላይ በቆየበት ጊዜ የተቀነሰ ሰራተኛ እንደሌለው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል ዕድሳት የተደረገለት ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለአጠቃላይ ዕድሳቱ 45 ሚሊየን ብር እንደፈጀ ተገምቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም