ብሄራዊ ፓርኮች ወሰኖቻቸውን በመከለል ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው-ባለስልጣኑ

2

ሰኔ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) ስድስት ብሄራዊ ፓርኮች ወሰኖቻቸውን በመከለል ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ጥበቃና ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን የዱር እንስሳት ለመጠበቅና ለመንከባከብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለአጋር አካላት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የባለስልጣኑ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ገብረ ሚካኤል እንደተናገሩት ብሄራዊ ፓርኮቹ ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ ድንበሮቻቸው ህጋዊ ሰውነት ያጋኙ ሰባት ብሄራዊ ፓርኮች እንደሚገኙ ጠቁመው የሰሜን ተራሮችና የአዋሽ ብሄራዊ ፓርኮች ህጋዊ ሰውነት ካገኙ ቀደምት ብሄራዊ ፓርኮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡

ህጋዊ ሰውነት ከሚያገኙት ብሄራዊ ፓርኮች መካከል የኦሞ፤ የገራይሌ፣ የያንጉደረስ፣ የአቢጃታና የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርኮች ጨምሮ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ እንደሚገኙበት አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

የብሄራዊ ፓርኮቹን ወሰን ለመከለል እንዲቻል ከአካባቢው ማህበረሰቦችና ከክልል መስተዳድሮች ጋር ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም “የፓርኮቹን ድንበሮች በአቅጣጫ መጠቆሚያ(ጂ ፒ ኤስ) በመከለል፣መለያ ምልክት በማቆም በህዝብ በማስተቸትና ሰነዱን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማጸደቅ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው” ብለዋል፡፡

ብሄራዊ ፓርኮች ድንበሮቻቸው ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ መደረጉ በፓርኮቹ የሚገኙ የዱር እንስሳት ከህገ ወጥ አደንና አደጋ ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንዲሁም ህገ-ወጦችን በህግ አግባብ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው ገልጸዋል፡፡

የፍትህ አካላት በብሄራዊ ፓርኮች ህገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋና እርሻን እንዲሁም ህገ-ወጥ አደንን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የህግ ቅጣት እንዲያገኙ መስራት ያስፈልጋል ያሉት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለአለም ፈንታሁን ናቸው፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ ተወካይ አቶ አበባው ታደሰ በበኩላቸው የፓርኩን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ከባለድርሻ አካላት ጋራ ተቀናጅቶ በመስራት በኩል ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

መድረኩ የፍትህ አካላት ከፓርኩ ጋር ተቀራርበው በመስራት በፓርኩ ክልል ውስጥ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን በጋራ ለመከላከልና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ በኩል አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞንና ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ የህግ አካላት እንዲሁም ከፓርኩ አዋሳኝ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡