አመራሩ የተጠሰውን ስልጠና ወደተግባር በመቀየር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ ስራ መስራት ይጠበቅበታል

2

ባህር ዳር ፣ሰኔ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) አመራሩ ስልጠናውን ወደተግባር በመቀየር ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተሟላ ሁኔታ መፍታት እንደሚጠበቅበት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር ገለጹ።

“አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ፣ አዲስ ሀገራዊ እምርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድድ የቆየው  የአማራ ክልል የብልጽግ ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ ለ6 ቀናት ሲሰጠው የቆየው ስልጠና ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር እንዳሉት የስልጠናው ዓላማ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር የተሰጠውን ሃላፊነት መወጣት እንዲችል አመራሩ የተሟላ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ማስቻል ነው።

በ6ኛ አገራዊ ምርጫ ብልጽግናን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም የአማራ ህዝብ ሲመርጠው ልማትንና መልካም አስተዳደርን እንዲያሰፍንለትና ህይወቱ እንዲሻሻል በመፈለግ ነው።

ህዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ተቀብሎ በመፍታት በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።

ችግር ፈጥኖ ለማስተካከል አመራሩን በአመለካከትና በአስተሳሰብ ማብቃት ተገቢ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል ላለፉት ስድስት ቀናት የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና በመስጠት አቅም የመገንባት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ህዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮችን በመረዳት በእውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄዎችን እንዲሰጡ የሚያስችል ስልጠና መሆኑን አስታውቀዋል።

አመራሩ ያገኘውን ስልጠና ወደስራ በመለወጥ የህዝቡን ጥያቄዎች የሚፈታ መሬት የነካ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።

በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚሰሩ ስራዎችን ለይቶ በመስራት የህዝቡን ኑሮ እንዲሻሻል አመራሩ የሚጠበቅብትን እየተወጣ ይሄዳል ነው ያሉት።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ እንዳሉት የህብረተሰቡን ተደጋጋሚ የማህበራዊና ኢኮኖሚያ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ወቅቱን የጠበቀ ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል።

ስልጠናው ከነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተነሳና የአመራሩን አቅም ለማጎልበት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የክልሉንና የአገሪቱን ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው።

ስልጠናው የባህር ዳር ስልጠና ማዕከልን ጨምሮ በአምስት የተለያዩ የስልጠና ማዕከላት ከሁለት ሽህ በላይ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።