ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ የሚወሰዱ መድሃኒቶች በተህዋሲያን መላመድ የጤና እክልን እያባባሱ ነው

5

ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ የሚወሰዱ መድሃኒቶች በተህዋሲያን መላመድ የጤና እክልን እያባባሱ መሆኑ ተገለጸ።

የጸረ-ተህዋሲያን ቀን በአገር ዓቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ ሲከበር እለቱ በውይይትና የተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቦ ውሏል።

በመድረኩ ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ ያለአግባብ መድሃኒቶችን መጠቀም የጸረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶችን በጀርሞች መለመድ በመፍጠር በጤና ላይ የሚፈጠሩ እክሎችን እያባባሰ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ሰይፉ፤ የጸረ-ተህዋሲያን መድሃኒት መላመድ ችግር በታዳጊ ሀገራት በስፋት እንደሚስተዋል አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ባደጉት ሀገራትም ጭምር ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸው በተለይም ተላላፊ የሆኑ ወረርሽኞች መስፋፋት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን በመጠቆም።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዓመት ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች በጸረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች ጀርሞችን መላመድ ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ መረጃዎችን አጣቅሰው ገልጸዋል።

መረጃው ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን እንደሚያመላክት አብራርተው በዚህ ረገድ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ፤ በኢትዮጵያ 50 በመቶ የሚሆኑ መድሃኒቶች ያለ ሃኪም ትእዛዝ ያለአግባብ  እንደሚወሰዱ በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ይህ ችግር በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት በሚሰጥ የመድሃኒት አጠቃቀም ላይም እንደሚስተዋል ገልጸው፤ ይህም በእንስሳት ተዋጽኦ ላይ ችግር እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናነት ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ በሽታዎች ተላላፊ መሆናቸውን ተከትሎ ሰዎች መድሃኒቶችን በዘልማድ የመውሰድ ልምድን እያዳበሩ መጥተዋል።

ይህም ለመድሃኒቶች በተህዋሲያን መላመድ ችግር መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የሰውና የእንስሳት የጤና አጠባበቅ የተሟላ አለመሆን፣ የመድሃኒቶች ሽያጭ ላይ ጥንቃቄ መጓደል፣ መድሃኒቶችን ያለ ጤና ባለሙያ ወይም ትእዛዝ መውሰድና መዋዋስ ለችግሩ መባባስ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለማቃለል የቁጥጥር ስርዓቱን በተሻለ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ለዚህም መድሃኒቶች ለገበያ ከመዋላቸው በፊት የጥራት ደረጃቸውን መመዝገብ፣ የማምረት ሂደትን መቆጣጠር የግብይት ሰንሰለቱ ላይ ክትትል ማድረግና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር ዋነኞቹ ናቸው ይላሉ።

በተጨማሪም ተገቢ የመድሃኒት አጠቃቀምን የሚያጎለብቱ መመሪያዎችን በማዘጋጀት የጤና ተቋማት እንዲጠቀሙበት የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን አክለዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ብቻ በሚደረግ ጥረት እንደማይፈታ ገልጸው የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።  

አግባብነት የጎደለው የመድሃኒት አጠቃቀም ለጉልህ የጤና ቀውስ ከማጋለጡ ባሻገር ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዓለም የጤና ድርጅት የዘርፉ የኢትዮጵያ ተወካይ መንግስተአብ ወልደአረጋይ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም ከወባ እና ከካንሰር ህመሞች ባልተናነሰ መልኩ የመድሃኒቶች በተህዋሲያን መላመድ ችግር የሞት መንስኤ ሆኗል ነው ያሉት።

የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማዳበር ጎን ለጎን ኢንፌክሽን የሚፈጥሩ በሽታዎችን መከላከል እና መፍትሔ አምጪ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ እንደሚገባ በመጠቆም።

የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች የሰው፣ የእንስሳትና የዕፀዋት ጤና የሚያውኩ ተህዋስያንን (Germs) በመግደል ወይም መራቢያቸውን በማስቆም ከተላላፊ በሽታዎች የሚጠብቁ ብሎም የሚታደጉ ናቸው፡፡

በፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርም መለመድ ችግርን መግታት ካልተቻለ  እ.ኤ.አ በ2050 ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ የሞት መንስኤ ሊሆን እነደሚችል ይገመታል።