ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ሳቢያ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የዊልቸርና የክራንች ድጋፍ አደረገ

91

ሰኔ 8/2014/ኢዜአ/ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጦርነቱ ሳቢያ በአማራና አፋር ክልሎች የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዊልቸርና ክራንች ድጋፍ አደረገ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በዛሬው ዕለትም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዊልቸርና ክራንች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም ለሁለቱም ክልሎች በድምሩ 430 ክራንችና 25 ዊልቸር ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

የድጋፍ ንቅናቄ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ወገኖች በጦርነቱ ጉዳት ለገጠማቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ፤ ካለው ችግር አንጻር በቂ ባይሆንም በሚኒስቴሩ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የሰሜኑ ጦርነት ያደረሰው ጉዳት ከአካልና ከንብረት አልፎ የስነ-ልቦና ጫናም ያስከተለ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም የተቻለውን ሁሉ እገዛና ድጋፍ ያድርግ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የአፋር ክልል የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ተወካይ አቶ መሃመድ ያሲን፤ በጦርነቱ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ የአካል ጉዳት ለገጠማቸው ወገኖች የተደረገ ድጋፍ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለቱም ክልሎች የደረሰው ውድመት መጠነ ሰፊ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ መልሶ ለመቋቋም በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም