የሱማሌ ክልል ገቢዎች ቢሮ ባለፉት አስር ወራት 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

8

ሰኔ 8/2014/ኢዜአ/ የሱማሌ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ ባለፉት አስር ወራት 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የሱማሌ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አህመድ ሙሁመድ፤ የገቢ አስባሰቡን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ባለፉት አስር ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 88 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ምንም እንኳን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ብልጫ ቢኖረውም በክልሉ የተከሰተው የድርቅ አደጋና የደረሰኝ ግብይት አነስተኛ መሆን ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እንዳላስቻለ ጠቅሰዋል።

ከነዚህ ችግሮች በተጨማሪም ከክልሉ ስፋትና ከግብር ከፋዩ ቁጥር ጋር ያልተመጣጠነ የገቢ መሰብሰቢያ ማሽን በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸርም የተሰበሰበው ገቢ የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለውና በቀሪ ወራቶችም ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ የተላለፈውን ጥሪ ተከትሎም የገቢዎች ቢሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ ግንባር ቀደም ለሆኑ ደንበኞቹ እውቅና እና ሽልማት ማበርከቱ የሚታወስ ነው።