የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

5

ደሴ፣ ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን አሳሰበ፡፡

ባለስልጣኑ በነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ዙሪያ በደሴ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

የባለስልጣኑ የነዳጅ አቅርቦትና ሎጅስቲክ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ሹመት እንደገለጹት፤ መንግስት በከፍተኛ ወጪ የሚያስገባው ነዳጅ ያለ አግባብ ለሁሉም በድጎማ ሲቀርብ ቆይቷል።

ከዚህ ባለፈም በኮንትሮባንድ መልሶ ከአገር እየወጣ እየተሸጠ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

መንግስት ለህብረተሰቡ ሲል ነዳጅን በድጎማ እያቀረበ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህ ወር እንኳ በዓለም ገበያ 78 ብር የሚሸጠውን ነዳጅ በ36 ብር እንዲሸጥ ቢወስንም በአጠቃቀም ጉድለትና በስግብግብ ነጋዴዎች የተነሳ አቅርቦቱ በችግር መፈተኑን ገልጸዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ሪፎርምና እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ሪፎርሙና እቅዱ በጥናት የተደገፈ የነዳጅ እጥረቱን፣ ኮንትሮባንዱን፣ ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይቱን፣ መጉላላቱንና በየማደያው የሚስተዋሉ ረጃጅም ሰልፎችን ለማስቀረት አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

በዚህ ለውጥ ጥቅማቸው የሚነካባቸው አካላት ችግር ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ጠቅሰው፤ ለሪፎርሙና እቅዱ ተግባራዊነት ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማውን ለመተግበር ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸው፤ በክልሎች በየደረጃው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

234 የነዳጅ ማደያዎች ያሉት የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቀለምወርቅ ምህረቴ በበኩላቸው የነዳጅ እጥረትና ብልሹ አሰራር በክልሉ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግርና የቅሬታ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሪፎርሙ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በመገንዘብም ክልሉ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ተግባራዊነትን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ተግባራዊነት ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የአፋር ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ተወካይ አቶ አህመድ መሃመድ ናቸው፡፡

ድጎማው ለሚመለከተው አካል ብቻ እንዲደርስ በማድረግ ክልሉ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።