የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ

4

ሰኔ 08 2014(ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ከዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ ምርታማነት እንዳይስተጓጎል በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከ2 ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ በድጋፉ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት በአካባቢው በተከሰተው የዝናብ እጥረት ማሳ ላይ ተዘርተው የነበሩት አዝዕርቶች ለምርት ሳይበቁ ቀርተዋል።

በዚህም ዩኒቨርስቲው የህዝቡን ችግር በማጥናት 750 ኩንታል የድንች፣በቆሎ፣ ቦሎቄ ፣የአትክልትና የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ዝርያዎቹ የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ያብራሩት ዶክተር ተስፋዬ ከዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን የምርታማነት ማነስ የሚታደጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ድጋፉ በሐረማያ ወረዳና አካባቢው በተከሰተው የዝናብ እጥረት ለተጎዱ 500 አርሶ አደሩች መከፋፈሉንና ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ነው የገለጹት።

ዩኒቨርስቲው ቀደም ሲል በዞኑ 9 ወረዳዎች ለሚገኙ ከ7 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች 460 ኩንታል የአትክልትና ሰብል ምርጥ ዘሮች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው አርሶ አደሩ የጀመረውን ምርታማነትን የማጎልበት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የሐረማያ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽኩሪ መሀመድ በበኩላቸው በወረዳው የዝናብ እጥረት በምርቱ ላይ የተከሰተውን ጉዳት ለማካካስ መንግስታዊና መንግሰታዊ ያልሆኑ ተቋማት ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ያደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍም ድርቅን በመቋቋም ምርት ለማግኘት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የምርጥ ዘር ደጋፍ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው የምርጥ ዘር ድጋፉ በዝናብ እጥረት በምርት ላይ የተከሰተውን ጉዳት ለማካካስ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።