ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች የአመራር ጥበብንና የአፈፃፀም ብቃትን በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው

86

ሰኔ 8/2014/ኢዜአ/ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች የአመራር ጥበብንና የአፈፃፀም ብቃትን በተግባር የሚያረጋግጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በትናንትናው እለት ከሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ከተከታተሉት ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢሶዴፓ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከለውጡ በኋላ የተመዘገቡ ውጤቶችን በትክክል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች የአመራር ጥበብንና የአፈፃፀም ብቃትን በተግባር የሚያረጋግጡ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በወጪ ንግድ እና ሌሎችም የተመዘገቡ ውጤቶች ተስፋ የሚጣልባቸው ጅምሮች መሆናቸውንም ፕሮፌሰር በየነ ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት አገርንና ህዝብን ለመለወጥና የስራ ባህልን ለማዳበር ለእያንዳንዱ ዜጋ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑንም ገልጸዋል።

የለውጡን ውጤት በማሳየት በተለይም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው ለተሻለ እድገት፣ ሰላምና ልማት በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የሙያና ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የምክር ቤቱን ስብሰባ የተከታተሉት ብርጋዴል ጀነራል ካሳየ ጨመዳ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍና በአገር ውስጥ በተፈጠሩ ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎች በአግባቡ ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከተረጅነት ወጥታ በምግብ ራሷን ለመቻል፣ ትውልድ ለማነጽ፣ በቴክኖሎጂና ሌሎችም ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችም የሚደነቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም