ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትብብር ይሰራሉ

152

ሰኔ 8/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትብብር የሚሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የናይጄሪያ አምባሳደር ቪክቶር አዴሌክ ገለጹ።

በአፍሪካ በህዝብ ብዛታቸው አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው የሚጠቀሱት ናይጀሪያ እና ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ በቅርቡ በናይጄሪያ በነበራቸው ጉብኝት የኢትዮጵያና ናይጄሪያን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ከፕሬዝዳንት ቡሃሪ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

የሁለቱ አገራት የረዥም ጊዜ ወዳጅነት በሁሉም መስኩ እንዲጠናከር የናይጄሪያም ፅኑ ፍላጎት መሆኑን በኢትዮጵያ የናይጄሪያ አምባሳደር ቪክቶር አዴሌክ ገልጸዋል።

አገራቱ ከእርስ በርስ ትብብራቸውም ባለፈ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ ኢንዳስትሪ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ባህልና ቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች በጋራ የሚሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አፍሪካ የሰላም ማዕከል እንድትሆን ናይጄሪያ የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያንም ተመሳሳይ ፍላጎት ስለምንረዳ ለዚሁ አላማ ስኬት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳትንና በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እየሰሩ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትብብር ይሰራሉ ብለዋል።

የናይጄሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካና የሊብሪካን የፔትሮሊየም ኢንዳስትሪን  እያንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው የኢንቨስትመንት ትስስራቸውን ያጠናክራሉ ብለዋል።

አገራቱ በፊልም ኢንዳስትሪም በትብብር በመስራት በናይጄሪያ ትልቁ የፊልም ኢንዱስትሪ ኖሊውድ የተሻለ ልምድ የሚገኝበት ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢትዮጵያና የናይጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እኤአ በ1960 ሲሆን ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በ1961 በአቡጃ ስትከፍት ናይጄሪያ ደግሞ በአዲስ አበባ በ1963 መክፈቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም