የባህል ፌስቲቫሉ በቀጠናው የተጠናከረ የባህል ትስስር እንዲኖር ያግዛል

229

ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የባህል ፌስቲቫል በቀጠናው የተጠናከረ የባህል ትስስር እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን በፌስቲቫሉ ላይ የባህል ምርቶችን ያቀረቡ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የባህል ፌስቲቫል በትላንትናው እለት በመስቀል አደባባይ "ጥበባትና ባህል ለቀጠናዊ ትስስር" በሚል መሪ ቃል ተጀምሯል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ የሕዝብ መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ምርቶች ለአውደ ርዕይ ቀርቧል፡፡

በዚህም ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የመጡ የባህል እሴቶች፤ ባህላዊ መድሀኒቶች፤ አልባሳት እና ባህላዊ ምግቦችም ቀርበዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው ባህላዊ ምርቶችን ይዘው የቀረቡ የአውደ ርዕይው ተሳታፊዎች ሁነቱ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሀረሪ ክልል የመጡት ወይዘሮ ኪምያ የሱፍ የሀረሪ ክልል መገለጫ የሆኑትን ባህለዊ ጌጣጌጦችና የእጅሰራ ውጤቶችን ፌስቲሻሉ ላይ ይዘው መቅረባቸውን ይናገራሉ።

ሁነቱ የክልሉን ባህላዊ እስቶችና ትውፊቶች ለሌሎች ለማስተዋወቅ እና እርስ በእርስ ግንኙነትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡

ሌላው ከአማራ ክልል የመጡት አቶ ፍስሀ እዘዘውም እንዲሁ፤ የባህል ፌስቲሻሉ መዘጋጀቱ እርስ በእርስ ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ሕዝቦችን የባህል ማንነትና መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን ይዘው የቀረቡት ደግሞ አቶ ጆን ጆይ ናቸው።

እሳቸውም ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ ምርቶችን ለማስተዋወቅ እና እርስ በእርስም ለመቀራረብ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጡት አቶ ሱሌማን አብዱላሂም፤ የምስራቅ አፍሪካ የባህል ፌስቲቫል የተጠናከረ የባህል ትስስሰር ለመፍጠር ያግዛል ነው ያሉት፡፡

የደቡብ ክልል ተወካዩ አቶ ዘላለም መርአዊ ሁነቱ የምስራቅ አፍሪካ ወንድማማቾች ትውውቅ የሚፈጥሩበት እና እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

''የባህል ፌስቲቫሉ የባህሎቻችን እና በርካታ ነገሮቻችን የምንለዋወጥበት እድል የሚፈጥርበት ነው'' ብለዋል፡፡

ፌስቲቫሉ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም