በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 20 በርሜል ነዳጅ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ

127

ጎንደር፣ ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታችአርማጭሆ ወረዳ በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 20 በርሜል ነዳጅ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢንስፔክተር ሙላት ጌጡ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ትናንት ከሰዓት በኋላ የተያዘው ህገ-ወጥ ነዳጅ ወደወረዳው ማዕከል ሳንጃ ከተማ ሊገባ የነበረ ነው።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-82862 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዚ የጭነት ተሸከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ ከተያዘው ነዳጅ ውስጥ 12 በርሜሉ ናፍጣ ሲሆን 8 በርሜል ደግሞ ቤንዚን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ ነዳጁን ጭኖ ሲያጓጉዝ ያገኘውን አሽከርካሪና አንድ ግለሰብ በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኢንስፔክተር ሙላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም