የሸኔ የሽብር ቡድን እና ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በጋምቤላ ከተማ በድንገት ከፍተውት የነበረው ጥቃት ከሽፏል

218

ሰኔ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)የሸኔ የሽብር ቡድን ራሳቸውን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር በማለት ከሚጠሩ ታጣቂዎች ጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ ከፍቶት የነበረው ድንገተኛ ጥቃት በጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት መክሸፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ጉዳዩን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ታጣቂዎቹ ወደ ጋምቤላ ከተማ ሰርገው በመግባት የህዝቡን ሰላም ለማወክና ለመዝርፍ ያደረጉት ሙከራ በክልሉና በፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት ከሽፏል።

የክልሉና የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎቹ ላይ በወሰዱት የተቀናጀ እርምጃ በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም አሁን ላይ የጋምቤላ ከተማ በሰላምና መረጋጋት ላይ ትገኛለች ብለዋል።የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ጥቃቱ እንዲከሽፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የጸጥታ ሃይሉና ህብረተሰቡ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።በከተማዋ አሁን ላይ ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በስተቀር ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ የማይቻል ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ኀብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅና የትኛውም አይነት አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥመው ደግሞ በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በመጠቆም ትብብር እንዲያደርግ ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌሎች አካባቢ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎችም ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢያቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በከተማዋ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ላደረሱት የህይወት ጉዳትም ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ መንግስት ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም