የ2015 በጀት ለብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮችና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስፈን ትኩረት ሰጥቷል

353

ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ2015 በጀት ለብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች እና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ማስፈን ትኩረት የሰጠ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባው ለ2015 በጀት ዓመት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጀት መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

በጀቱን በሚመለከት የገንዘበ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።

የበጀት መግለጫ ከ786 ቢሊየን ብር ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 347 ነጥብ 12 ቢሊዮንብር እንዲሁም ለካፒታል ወጪ 218 ነጥብ 11 ቢሊዮን መመደቡን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ የ2015 በጀት ዓመት የበጀት እቅድ ለ10 ዓመቱ የልማት እቅድ መሳካት ስለሚኖረው ሚና ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የ10 ዓመቱ እቅድ በ2013 በጀት ዓመት ይፋ ከሆነ በኋላ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ቀወሶች በሀገሪቱ ላይ ፈተና መደቀኑን ተናግረዋል።

እቅዱን በማስፈፀም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጦርነት እንዲሁም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት አሁንም ድረስ ጫና ፈጥረዋል ብለዋል።

በመሆኑም የ2015 በጀት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትራስንፎርሜሽን፣ ለዘላቂ ልማት ግቦች፣ የግብርና፣ የኢንዱስተሪ ምርታማነትን እንዲሁም የኤክስፖርት ንግድን  ለመጨመርና ለስራ እድል ፈጠራ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በጀቱ ሲዘጋጅ በካፒታል ወጪም ሆነ በመደበኛ በጀት ከ2014ቱ ጋር ሲነጻጸር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጥ ከፍተኛ ጭማሪ እንደተደረገም ገልጸዋል።

በ10 ዓመቱ እቅድ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች የሚባሉት ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይሲቲ በበጀቱ ከፍትኛ ትኩረት እንደተሰጣቸው አብራርተዋል።

በዚህም ለካፒታል ወጪ ከተመደበው 218 ቢሊየን ብር 61 በመቶው ለብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች መመደቡን ገልጸዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ማህበራዊ ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጡ እንደ ትምህርት፣ ጤና ሌሎችም ዘርፎች ከካፒታል በጀቱ 22 በመቶ የሚሆነው እንደተመደበላቸው ተናግረዋል።

በጀቱ የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦች ለማሳካት የታቀዱ ዘርፎችንም ታሳቢ ማድረጉን ገልጸው፤ በዚህም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስፈን እንደሚሰራ ገልዋል።

የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስፈን ሀገሪቱ ያለባትን የውጭና የሀገር ውስጥ እዳ በአግባቡ ማስተዳደርና መክፈል እንደሚገባትም ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻር ከመደበኛ በጀቱ ውስጥ 50 በመቶው ለእዳ ክፍያና ሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ ግቦች እንደሚውሉም ገልጸዋል።

ከዚህም 72 በመቶው ቀጥታ ለእዳ ክፍያ እንደሚመደብ በማንሳት የ10 ዓመቱን እቅድ ለማሳካትም ለክልሎች 209 ቢሊየን ብር ድጎማ መመደቡን ተናግረዋል።

ለአነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ስራዎች እንዲሁም ለግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች 12 ቢሊየን ብር ለክልሎች መመደቡን ጠቁመዋል።

በጀቱ የ10 ዓመቱን የልማት እቅድ ከማሳካት አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥም ሆኖ በ2014 በጀት ዓመት መጨረሻ የ6 ነጥብ 6 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብበት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም