የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት በ11 ወራት ውስጥ ከ313 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ሰብስቧል

41

ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ ከ313 ሺህ 793 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአለም ደም ለጋሾች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ “ደም መለገስ የአብሮነት ተግባር ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ለ19ኛ ግዜ በ ጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ትናንት ተከብሯል።

በመድረኩም ከ37 እስከ 70 ጊዜ ድረስ ደም የለገሱ በጎ ፈቃደኞችና በዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የባህር ዳር፣ አዳማና ጅግጅጋ ደም ባንክ ቅርንጫፎች ምስጋናና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ቀኑን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ለጤና ስርዓት መጠናከር የበኩላቸውን እገዛ እያደረጉ ናቸው።

ከዚህ በፊት በአጠቃላይ ከ300 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ተለግሶ የማያውቅ ሲሆን አሁን የተመዘገበው ከፍተኛው እንደሆነ ገልጸዋል።

የተገኘው የደም መለገስ ቁጥር እምርታ ቢያሳይም በአለም ጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት የአንድ ሀገር ህዝብ ቢያንስ አንድ መቶኛው ደም መለገስ አለበት ነገር ግን በሀገሪቱ አሁን የተገኘው የደም መጠን የጤና ድርጅቱን መለኪያ ቁጥር የማይጠጋ ነው፡፡

መጪው ግዜ ክረምት በመሆኑ ትምህርት ቤቶች የሚዘጉ በመሆናቸው እና የዝናቡ ሁኔታ ደም ለመለገስ አዳጋች ስለሚሆን የደም እጥረት እንዳይገጥም ህብረተሰቡ ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ