ወደ ውጭ ከተላከ 261 ሺህ ቶን ቡና 1 ነጥብ 2 ቢለዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

2

ሀዋሳ፤ ሰኔ 08/2014 (ኢዜአ)፡ ባለፉት 11 ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 1 ነጥብ 2 ቢለዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በቡና ዘርፍ ለተሰማሩ ላኪዎች፣ አቅራቢዎችና ባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ትናንት በሐዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሻፊ ኡመር እንደገለጹት፣ ገቢው የተገኘው ባለፉት 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 261 ሺህ ቶን ቡና ምርት ሽያጭ ነው።

ባለፈው በጀት ዓመት 248 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው፤ “ከግብይት ስርዓቱ ለውጥ በኋላ ገቢው እያደገ መጥቷል” ብለዋል።

የግብይት ስርዓቱ ለውጥ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንዳስገኘ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተራዘሙ የእሴት ሰንሰለቶችን በማሳጠር አቅራቢና ላኪዎችን ማገናኘት ማስቻሉን ገልጸዋል፡።

“በተጨማሪም የቡና ጥራትን በመጠበቅ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ በላይ ግብይቱን በማዘመን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አድርጓል” ብለዋል።

በቀጣይም የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምርት ጥራትን ማስጠበቅና ግብይቱን በማዘመን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በባለስልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ታጠቅ ግርማ በበኩላቸው፣ በቡና ግብይቱ የተደረገው ለውጥ በአንድ ቦታ ብቻ የተወሰነውን ሀገር አቀፍ የቡና ግብይት ያስቀረ ነው ብለዋል።

አሰራሩ ከቡና አምራች ሀገራት በተወሰደ ልምድ አማራጭ የግብይት ቦታዎችን በመፍጠር የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠሩን ገልጸዋል።

እሴት ከማይጨምሩ አካላት ለመለየት የሚያስችል አሰራር መሆኑንም ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ ምርቱን በጥራት እንዲያዘጋጅ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተጨማሪ አማራጭ የግብይት ስርዓት በመፍጠር አርሶ አደሩ ላኪ እንዲሆን ጭምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

አሰራሩ ላኪ እና አቅራቢ ያለማንም ጣልቃ ገብነት መገበያየት እንዲችሉ በማድረግ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተንዛዘ አሰራር በማስቀረት ጊዜ፣ ገንዘብና ወጪ እንደሚቆጥብ አመልክተዋል።

መድረኩ የግብይት ስርዓቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያሉበትን እጥረቶች በማስወገድ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዘርፉ የተደረገው ለውጥ የተዛባውን የቡና ግብይት ስርዓት ከማስተካከል ባለፈ የቡና ምርታማነት ማሳደጉን የገለጹት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ የሲዳማ ክልል ቡና አቅራቢዎችና አበጣሪዎች ዘርፍ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የምርት ገበያ የግብይት ስርዓት አማራጮችን የማያስቀምጥ በመሆኑ በርካታ የዘርፉን ተጠቃሚዎች ተጎጂ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ከሁለት ዓመታት ወዲህ የቀጥታ ግብይት ስርዓት በመፈጠሩ 90 ከመቶ የክልሉ አምራችና አቅራቢ ትስስር ፈጥረው ግብይት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከአርሶ አደሩ ቡና የሚረከበው አቅራቢ ዘንድ ያለውን የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት ችግር መፍታትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አሰራሮችን መከተል ከተቻለ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ  ማሳደግ ይችላል ብለዋል።ለአንድ ቀን በቆየው መድረክ ከሲዳማ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች የቡና ላኪዎች፣ አቅራቢዎችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በግብይት ስርዓቱ በተገኘው ውጤትና ተግዳሮት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡