የምስራቅ አፍሪካ የባህልና የጥበብ ፌስቲቫል መካሄዱ ለጋራ መዳረሻችን በጋራ እንድንነሳ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል

ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የባህልና የጥበብ ፌስቲቫል መካሄዱ ለጋራ መዳረሻችን በጋራ እንድንነሳ አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚንስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

ፌስቲቫሉ "ጥበባትና ባህል ለቀጠናዊ ትስስር" በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል።

የፌስቲቫሉ መዘጋጀት ለቀጠናው የህዝብ ለህዝብ ትስስር እና ለባህል ዲፕሎማሲ መጎልበት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።

መርሃ ግብሩን በማስመልከት ንግግር ያደረጉት የባህልና እስፖርት ሚንስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፤  ለጋራ መዳረሻችን በጋራ እንድንነሳ ፌስቲቫሉ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ የባህልና የጥበብ ፌስቲቫል ለቀጣናዊ ውህደት እንደ መግቢያ በር ሆኖ ያገለግላል ሲሉ ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሁለንተናዊ ትስስር በማጠናከር በጋራ ለማደግ ለሚደረገው ጥረትም አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

የባህልና የጥበብ ሀብቶችን በመጠቀም ባለሃብቶችን በምስራቅ አፍሪካ እንዲያለሙ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ እንድህ አይነት ኩነቶች በዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የባህልና ስፖርት ሚነስቴር ፌስቲቫሉ እነዲዘጋጅ በማድረግ ላደረገው አስተዋጽኦም ሊመሰገን ይገባዋል ነው ያሉት።

የደቡብ ሱዳን የበህል ሚንስቴር ተወካይ ኩአች ዌክ ዎል፤ በበአሉ በመታደማቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ገለጸዋል።

ፌስቲቫሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ህዝቦችን ይበልጥ በማቀራረብ የባህልና ማህበራዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር አስፈላጊ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም