በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚሰራጩ አፍራሽ መልዕክቶችን ለመመከት ተባብሮ መሥራት ይገባል-ምሁራን

91

ወልዲያ፤ ሰኔ 07/2014 (ኢዜአ) በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚተላለፉ አፍራሽ መልእክቶችን ለመመከት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ምሁራን ገለጹ፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን  እንደገለጹት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩና እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት በሀገር ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።


ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በተሰራው ዘርፈ-ብዙ ሴራ የአንድነት ተምሳሌት ሆና ስትጠቀስ በነበረችው ሀገር ግጭቶች እንዲፈጠሩ መደረጋቸውን  ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት  መምህር አቶ ጥላሁን አረጋ እንዳሉት ለሀገርና ህዝብ ደንታ በሌላቸው አካላት በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ለግጭቶች መባባስ ምክንያት ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት በተደራጀ አግባብ በተሰራ አፍራሽ እንቅስቃሴ ግጭቶች መስፋፋታቸውንና በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

እነዚህ አፍራሽ አካላት በአሁኑ ወቅት  ለፖለቲካ ዓላማና ለገንዘብ ማግኛ፤ በፌስቡክ ፤በዩቲዩብና መሰል የማህበራዊ ትስስር ገጾች የሕዝቡን ደህንነት ስጋት ላይ ለመጣል ሲሯሯጡ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ እነዚህ አካላት  የሀሰት መረጃ ከማሰራጨት ውጭ ጋዜጠኝነት የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ሥነ-ምግባር ያልተላበሱ ፤ለገንዘብና ለእኩይ ዓላማ ለማስፈጸም  የቆሙ  መሆናቸውን በመገንዘብ ጊዜውንና ጆሮውን ሊሰጣቸው አይገባም ብለዋል፡፡

መንግሥትም የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ አካላትን በሕግ  እንዲጠየቁ  ከማድረግ ባለፈ፤ትክክለኛ መረጃዎች  በፍጥነት እንዲደርሱ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

ለወጣቱ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የማህበራዊ ትስስር ገጾች አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን ማሳወቅ  እንደሚጠበቅ አመልክተው፤ እሳቸውም በሚያስተምሩበት ሙያ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ሌላው የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት መምህሩ አቶ ሀብታሙ ሙሉጌታ በበኩላቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾች  በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ተናግረዋል፡፡

ማህበራዊ ትስስር ገፆች በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ ማህበረሰብን በማንቃት ሀገራዊ ልማትና አንድነት ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላለች ሀገር ሕዝብንና መንግሥትን የሚያቀራርቡ ለሀገራዊ ለውጡ እርሾ ሊሆኑ የሚችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችን መፃፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ማህበራዊ የትስስር ገጾች አጠቃቀማቸው ገደብ አልባ በመሆኑም ለሀገር አለመረጋጋትና ግጭት መፈጠር ምክንያት መሆናቸውን አመልክተው፤እነዚህን አጥፊዎች በመለየት መጠየቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ምሁራኑ  ከመደበኛው የማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የተሳሳተ አዝማሚያ ተማሪዎች እንዲገነዘቡት የማድረግ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም