የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ7 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ገለጸ

91

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ7 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማስመልከት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ችግኙ የሚተከለው በመንግስት ሰራተኞች፤ በህብረተሰቡ ተሳትፎና በተቋማት ነው፡፡

የአስተዳደሩ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ፤ በዘንደሮው የአረንጓዴ ልማት በአስተዳደሩ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የከተማዋን ውበት፡ ስነ-ምህዳር፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም የጽደቀት ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ችግኞቹ ለተከላ የተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረውን 'ምግባችን ከጓሮችን' መርሃ ግብር ታሳቢ ያደረጉ የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን ያካተተ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ለዚህም መሳካት አብይ ኮሚቴና የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱን ያነሱት ምክትል ኃላፊዋ  ጉለሌ እፅዋት ማዕከልን ጨምሮ በአስር በተለያዩ ቦታዎች ችግኞችን የማፍላት ስራ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች በማህበራት ተደራጅተው ያዘጋጇቸውን ችግኞች ለመጠቀም የሚያስችል ስራ መሰራቱንና ከተለያዩ ክልሎች ማስገባት የሚቻልበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አክለዋል።

በከተማው ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ26 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል መቻሉን አስታውሰው ዘንድሮ ደግሞ ከ7 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የችግኝ የጽድቀት መጠንም 80 ከመቶ በላይ መሆኑን ጠቅሰው ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት ሁሉም ህብረተሰብ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

'ኢትዮጵያን እናልብሳት' በሚል መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የችግኝ ተከላ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በአራተኛ አመት መጨረሻ ላይ ከ20 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም