የሐዋሳ ከተማን ማራኪ፣ ጽዱና ምቹ ለማድርግ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል-ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ

164

ሀዋሳ፤ሰኔ 7 ቀን 2014 ((ኢዜአ) ) በሐዋሳ ከተማ ህገ ወጥ ግንባታና የመንገድ ላይ ንግድን በመከላከል ከተማዋን ማራኪ፣ ጽዱና ምቹ ለማድረግ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሰራ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ አሳሰቡ።

ከተማ አስተዳደሩ በህገ ወጥ ግንባታና ንግድ እንዲሁም በከተማዋ ጽዳትና ውበት ላይ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ  ዛሬ በሐዋሳ ተካሂዷል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንደገለጹት በከተማዋ ከፕላን ውጭ ግንባታ፣ ህገ ወጥ ንግድ፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ።

ህገ ወጥ ግንባታና ንግድን ከመከላከል ባለፈ ከተማዋን ማራኪና ጽዱ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ሐዋሳን ዋነኛ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ያሉት ከንቲባው፤ በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የከተማዋን አካባቢዎች የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ከከተማዋ ማስተር ፕላን ውጪ የተካሄዱ ህገ ወጥ ግንባታዎችን፣ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶችን በሸቀጦች የሚዘጉ ነጋዴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማዋን እድገት በሚጻረር መልኩ የሚካሄዱ ማናቸውም የግንባታ፣ የንግድና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዲሁም በዘፈቀደ የሚጣል ቆሻሻን ለማስቆም የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ሐዋሳ ከተማን ለመኖሪያና ለኢንቨስትመንት ምቹ በማድረግ የከተማውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ በበኩላቸው ከተማዋ  በጎብኚዎች ተመራጭ መሆኗን ተናግረዋል።

"ተመራጭነቷን ለማስቀጠል ጽዳትና ውበቷን ከመጠበቅ ባለፈ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን መግታት" ይገባል ብለዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር ህገወጥ እንቅስቃሴን በማስቆም ከተማዋን የተሻለች ለማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ አደርጎ እንዲሰራ ታስቦ መድረኩ  መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ከተማዋን ፅዱ፣  ውብ እና ማራኪ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጠየቁት ደግሞ ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ ናቸው።

ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥ ንግድን ጨምሮ ለከተማዋ ልማትና እድገት ማነቆ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር  የህግ የበላይነትን እንደሚያስከበር አስታውቀዋል።

በሐዋሳ ታቦር ክፍለ ከተማ የኮጋኖ ዋጮ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ማርቆስ ኤልያስ በበኩላቸው፣ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ለማስጠበቅና ህገ ወጥ ግንባታዎችን ለመከላከል  ህብረተሰቡን በማስተባበር  ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ የሁሉም ሴክተር ቢሮ ሃላፊዎች፣የቀበሌ ሊቀ-መናብርትና የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጆች መሳተፋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም