በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የገበያ ጉድለት መሙላት የሚያስችል ሥራ መስራት አለባቸው

4

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 07/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የገበያ ጉድለት መሙላት የሚያስችል ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከሚገኙ የልማት ድርጅት አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፤ መንግሥት በልማት ዙሪያ ያለውን ፍላጎትና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ለይቶ በማወቅ የተናበበ ተግባር መፈጸም አስፈላጊ ነው።

የልማት ድርጅት አመራሮች ከተለመደው አሰራር በመውጣት ለውጤት የሚያበቃቸውን አዲስ አስተሳሰብና ስልትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ነው ያሳሰቡት።

ድርጅቶቹ በንግድ ሥርዓት ሞዴል መመራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ውጤታማነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በመጠቀም ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን መከተል አለባቸው ብለዋል።

ይህ ሲሆን የልማት ድርጅቶቹ የገበያ ጉድለትን መሙላት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚደርሱ ነው የገለጹት።

ይህ ብቻ ሳይሆን እነዚህ የልማት ድርጅቶች ግልጽ የሆነ የንግድ ሥራ እቅድ አዘጋጅተው መመራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

ድርጅቶቹ  ሁልጊዜ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ገበያ በማምጣት ጎልተው መታየት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በእንደዚህ አይነት መልኩ የሚመሩ ከሆነ ከአገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑም አክለዋል።

ሁሉም የልማት ድርጅት የአንድ ገጽ እቅድ እንዲያዘጋጅና ለክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ማቅረብ እንዳለበትም ፕሬዝዳንቱ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ሁሉም የልማት ድርጅቶች ፈጻሚ አካላት አፈጻጸምን መሠረት ያደረገ ግምገማ በየሦስት ወር እንዲካሄድም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል ያወጣቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እቅድ ለማሳካት የልማት ድርጅቶች ውጤትን ያማከለ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩም አቅጣጫ ተቀምጧል።