የጋዜጠኝነት ሙያን የወንጀል መሸፈኛ፤ የሕገ-ወጥ ጥቅም ማካበቻ ማድረግ ተገቢነት የለውም

2

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋዜጠኝነት ሙያን የወንጀል መሸፈኛ፤ የሕገ-ወጥ ጥቅም ማካበቻ ማድረግ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በኢትዮጵያ 5 ሺህ 860 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሳላቸው ጥያቄዎች መካከል የጋዜጠኞች የእሥራት ሁኔታ አንዱ ነው።በጋዜጠኞች ላይ መታሰር ብቻ ሳይሆን በቁጥጥር ሥር የሚውሉበት መንገድም ትክክል አይደለም የሚሉ ጉዳዮች ተነስተዋል።

ለእነዚህና ሌሎችም ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቷ ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሃይማኖት፣ በብሔርና ሌሎችም ምክንያቶች ለማጋጨት እየሰሩ፤ የአገር መከታ የሆነውን ሰራዊት እያንቋሸሹ ያሉ አክቲቪስቶች በህግ ሲጠየቁ በጋዜጠኛ ስም ሽፋን ማድረግ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ ባወያየበት ወቅት ሕዝቡ በስፋት ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ባነሳው ጥያቄ መሰረት መንግሥት ሕግ በማስከበር ላይ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሕግ ማስከበር ሥራው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሱማሌ ክልሎች በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።በዚህ ሂደት ውስጥ ያጋጠመው አክቲቪስት (የማኅበረሰብ አንቂ)፣ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ የመለየት ጉዳይ ችግር አጋጥሟል ነው ያሉት።

በተለይም ከማሕበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሰዎች ብዙ ገቢ ለማጋበስ ሲሉ ወንጀል እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ አክቲቪስቶች ሕዝቡን እርስበርስ የሚያጋጩ ተግባራት ላይ ተሳትፈው በሕግ ሲጠየቁ “ጋዜጠኛ” በሚል ሽፋን ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የለውም፤ ሕግ የሚተላለፍ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የተቋማትን ስም የሚያጠፉና የሕዝብ አንድነትን የሚሸረሽር ተግባር ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች ‘አክቲቪስትም፤ ጋዜጠኛ’ በማለት ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም ብለዋል።”በየትኛውም መመዘኛ ሕዝብን የሚያባላ ተግባር ውስጥ የሚሳተፍ ማንም ሰው በሕግ ተጠያቂ ይሆናል” ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ያላግባብ በሕግ ጥላ ሥር የዋሉ ግለሰቦች ካሉ ሊፈተሽ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።በተመሳሳይ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ሚዲያ ተዳክሟል’ የሚለው አነጋገር ትክክል አለመሆኑንና ከለውጡ ወዲህ ሚዲያ እያደገ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በኢትዮጵያ 5 ሺህ 860 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የግጭትና ጦርነት አካሄድ ከመደበኛ ውጊያ ወደ ሳይበር ጥቃት እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በየቀኑ በቢሊዮን ዶላር በሚቆጠር ሃብት ላይ የሳይበር ጥቃት እየደረሰ መሆኑን አብራርተው፤ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በኢትዮጵያ 5 ሺህ 860 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡የሳይበር ጥቃቶችም ታላላቅ የልማት ተቋማት ላይ ትኩረት ያደረጉ እንደነበሩም ጠቅሰዋል፡፡

ከተፈጸሙት የሳይበር ጥቃቶች መካከል አብዛኛውን በማክሸፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብት መከላከል መቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡በመሆኑም በቀጣይ ከመደበኛ የሰራዊት ግንባታ ጎን ለጎን የሳይበር ጥቃትን የሚከላከል አቅምን ይበልጥ በመገንባት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ይሰራል ነው ያሉት፡፡