ሀገራዊ ምክክሩ መላ ኢትዮጵያውያንን በሚጠቅም መልኩ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ያስችላል

145

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 07 ቀን 2014(ኢዜአ) ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ከሆነ መላ ኢትዮጵያውያንን በሚጠቅም መልኩ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ አካታች ሀገራዊ ምክክሩ ሲሆን በምክክሩ በመደማመጥና በተሻለ ሀሳብ ኢትዮጵያን የሚያፀና ስራ ለመስራት ግብ መያዙን ጠቁመዋል።

የሀገራዊ መግባባት ጉዳይ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ለረጅም ዓመታት በተለያዩ ወገኖች ሲጠየቅ እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም በመንግስት ደረጃ ማን ከማን ተጣልቶ ነው ሲሉ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ከለውጡ ወዲህ መንግስት እንመካከር ብሎ ሲጠይቅ ደግሞ አሁንም አንዳንድ ወገኖች አንነጋገርም እያሉ ህዝብ እያምታቱ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስራ እንዲሰራ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጸዋለ።

በዚህም ኮሚሽኑ የማቋቋም ሃላፊነትን ለህዝብ ተካዮች ምክር ቤት መስጠቱ፣ አጀንዳ መወሰንን የኮሚሽኑ ተግባር ማድረጉ እንዲሁም በምክክሩ የተሳታፊዎችን መጠን የመወሰን ስልጣን ለኮሚሽኑ መሰጠቱ መንግስት በቀናነት የፈቀዳቸው ውሳኔዎች ናቸው ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለኮሚሽኑ በሀገር ደረጃ አንቱ የተባሉና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በመሾሙ ምስጋና ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኮሚሽነሮቹ ስራና ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ሁሉም እንዲተባበር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀውን ይወስናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክክሩ በይፋ የሚደረግና መቀራረብን ታሳቢ ያደረገ እነዲሆን መንግስት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

"በሀገራዊ ምክክሩ የማይሳተፉ አሉ ወይ" በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ሀገራዊ ምክክር ሲፈቀድ አንሳተፍም የሚሉና የስልጣን ምንጩ የህዝብ ድምፅ መሆኑን የማያውቁና በሌላ አማራጭ ለመቀጠም የሚፈልጉ ሃይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋናው በሽታ "ፖለቲከኞች ሀገሪቱ የእነሱ በቻ፣ ወሳኝ እነሱ ብቻ፣ ተራው ዜጋ በሀገሩ ጉዳየ መብት ያለው አይመስላቸውም፤ እነሱ ብቻ ትክክል የሆኑ ይመስላቸዋል። መገለጫቸው ሴራ ቅጥፈትና ተንኮል ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ለመላ ኢትዮጵያውያን የሚጠቅም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ምክክሩ በተሳካ ሁኔታ ከተካሄደ ጠንካራ ሀገር እውን ለማድረገ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር አድካሚ ስራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከስድብና አቃቂር በመውጣት ሁሉም በየአቅሙ ሀሳቡን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት የተሻለውን ለሀገር ጥቅም ማዋል ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም