በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ውጤታማ ስራ ለማከናወን አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

51

ሐረር ፤ ሰኔ 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በዘንድሮ “የአረንጓዴ አሻራ” መርሃ ግብር የተሻለና ውጤታማ ስራ ለማከናወን አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ። 

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላን ስኬታማ ለማድረግ  የተቋቋመው እስትሪንግ ኮሚቴ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መጀመር በክልሉ የተመናመኑ ደኖችን በመተካትና ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ እገዛ እያደረገ ነው።

በዘንድሮ ዓመትም “በአረንጓዴ አሻራ” የችግኝ ተከላን ለማከናወን የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የዝግጅት ስራዎች በቢሮ፣ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና በማህበረሰቡ እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ የችግኝ ማፍላት፣ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮ እና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች በዘመቻ እና በተናጠል ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በተለይ አመራሩና የዘርፉ ተቋማት ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገምና ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ለዘንድሮው ስራ የተሻለ ስራ ለማከናወን መዘጋጀት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

አመራሩ ህብረተሰቡን በማስተባበርና ሁኔታዎችን በማመቻቸት የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ አቶ ኦርዲን አሳስበዋል።

የክልሉ የዘርፍ ተቋማትና ወረዳዎች በእቅድ በመመራት፣ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ሌጋሲ ለማስቀጠል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ  ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን እንዳስገነዘቡት በክልሉ በዘንድሮ “የአረንጓዴ አሻራ” መርሃ ግብር የተሻለና ውጤታማ ስራ ለማከናወን አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል።

“የአረንጓዴ አሻራ” በክልሉ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ስለሚያግዝ አመራሩ  በትኩረት እንዲሰራም ሲሉ አቶ ኦርዲን በአፅንኦት አሳስበዋል።

በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት ከ7 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ከ67 በመቶ የሚበልጡት መጽደቃቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ገልጸዋል።

በዘንደሮ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር በክልሉ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ወይዘሮ ሚስራ ተናግረዋል።

በክልሉ በሁሉም የገጠርና ከተሞች ቀበሌዎች በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለይ ምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የታዩ ተግዳሮቶችን በማስወገድ፤  አበረታች ስራዎችን በማጎልበት የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤታማና ስኬታማ ለማድረግ  ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

የስትሪንግ ኮሚቴው አባላትም በተለይ በመርሃ ግብሩ የሚተከሉ ባለቤት አልባ ችግኞች መኖራቸውን፣ የውሃ አቅርቦትና ከእንክብካቤ አንጻር የጽድቀት መጠን ችግር መታየቱን አመልክተዋል።

እንዲሁም ስራውን የአንድ ወቅት ብቻ ማድረግ፣ በኃላፊነት አለመንቀሳቀስ፣ የክትትል አለመጠናከርን እንደ ችግር አንስተው  በዚህ ላይ አመራሩ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።