''ህግ የማስከበር ዘመቻው ህዝብ ሲያነሳ ለነበረው የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል''

121

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''ህግ የማስከበር ዘመቻው ህዝብ ሲያነሳ ለነበረው የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አህመድ ተናገሩ፡፡

በዘመቻው ከ5 ሺህ በላይ በየደረጃው ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ላይ ከእስር ጀምሮ ከስራ እስከማባረር የደረሰ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ነው ያነሱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ህግ የማስከበር ስራው የተጀመረው ህዝብ ሲያነሳው ለነበረው ተደጋጋሚ የሰላም ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ያካሄደውን አንደኛ ጉባኤ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ከህዝብ ጋር ባደረገው ውይይት የሰላምና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የኑሮ ውድነት ጥያቄ በስፋት መነሳቱን አብራርተዋል፡፡

በተለይ በአማራ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች የሰላም ጥያቄን በስፋት ሲያነሱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም መሰረት መንግስት ውጤታማ የህግ ማስከበር ስራ ማከናወኑን ጠቅሰው ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መንግስት እያካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል 3 ሺህ 500 የሚሆኑ መሳሪያ ይዘው የከዱ የሰራዊት አባላት መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት።

ህዝብን በመዝረፍ፣ ሴቶችን በመድፈርና ሰላምን በማወክ ተግባር ሲሳተፉ እንደነበር አስታውሰው ለህግ የበላይነት መከበርና ለህዝብ ሰላም ሲባል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ከ5 ሺህ በላይ በየደረጃው ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ላይ ከእስር ጀምሮ ከስራ እስከማባረር የደረሰ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይፈልጉ አካላት ጋዜጠኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች እንደታሰሩ በማስመሰል ህግ የማስከበር ሂደቱን ጥላሸት ለመቀባት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

አገርና ህዝብን አደጋ ላይ በሚጥሉ ተግባራት እየተሳተፉ ያሉ ጋዜጠኛ ነኝ ማለት ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም