ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በመንገድ፣ በቴሌኮም፣ በአየር መንገድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስደናቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል

2

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በመንገድ፣ በቴሌኮም፣ በአየር መንገድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስደናቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራራያቸው በለውጡ ሂደት በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በዚሁ ሁኔታ ውስጥ የተመዘገቡ ውጤቶች አስደማሚ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ክስተቶች በአገራዊ ሪፎርሙ ላይ ፈታኞች ነበሩ ብለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ በተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ኢትዮጵያዊያንን ያግባባ ግድብ ነው በሚል ቃል አንድነት ታይቷል፤ ይህም ለውጡን የምንመራበት ቃል ነው ብለዋል።

‘የነገሮች ሁሉ መሰረትና እንደ ዘር ሆኖ የሚያገለግል ሃሳብ ነው’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ያለው ሰው ተቋምን እንደሚገነባ ሁሉ ተቋም ደግሞ አገር ይገነባል፤ በዚህ ዐውድ አገር እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

በመንገድ መሰረተ-ልማት ረገድ በመንገዶች አስተዳደር በኩል ብቻ 13 ሺህ ኪሎ ሜትር የነበረው የአስፓልት መንገዶች በሦስት ዓመት ብቻ 4 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር መንገዶች የተገነቡ ሲሆን 8 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ አሁን ላይ እየተገነባ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል 9001 ኪሎ ሜትር ባጀት ጸድቆለት በተለያየ ምክንያት ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል 9 ሺህ በጸጥታ ምክንያት አልተጀመረም ብለዋል።

በተለይም ምርታማ አካባቢዎች ላይ በመለየት በልዩ ሁኔታ የመንገድ መሰረተ-ልማት እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል 151 ኪሎ ሜትር የአስፓልት እንዲሁም 470 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገድ መገንባቱን ገልጸዋል።

በትራንስፖርት ረገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ብዛቱን በ33 በመቶ ማሳደጉን፤ መዳረሻውንም ወደ 135 ማሳደጉን፣ ቦሌ ኤርፖርት ደንበኞችን የማስተናገድ አቅሙን ከ6 ሚሊየን ወደ 22 ሚሊዮን  ማሳደጉን ገልጸዋል።

በቴሌኮም መሰረተ-ልማት ረገድ አሁን ላይ ኢትዮ-ቴሌኮም 65 ነጥብ 5 ሚሊዮን ደንበኛ በማድረስ 27 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞች ማፍራቱን፣ 55 ቢሊየን ገቢ በማድረስ ትርፉን በ21 ቢሊየን ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።

በአገልግሎቱም ተመጣጣኝ አገልግሎት እየሰጠና በቴክኖሎጂ እየዳበረ መምጣቱን ገልጸው፤ ለአብነትም  በዓመት 20 ቢሊየን ብር ያገበያየውን በቴሌብር ግብይትን ማስተናገዱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አብዛኛው የክፍያ አገልግሎት ወደ ቴሌብር እየገባ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቴሌኮም ዘርፍ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በስኳር ፋብሪካዎች ረገድም አራት የነበሩት ፋብሪካዎች  አምስት በመጨመር አሁን ላይ ወደ ዘጠኝ ፋብሪካዎች ማደጉንና የስኳር ምርቱም 360 ሺህ ቶን መድረሱን ገልጸዋል።

በትምህርት መሰረተ-ልማትም ከለውጡ በኋላ ከመዋለ-ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ 2 ሺህ 150 ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ረገድ ከለውጡ በኋላ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ጨምሮ 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት መቻሉን አውስተዋል።

አምራች አንዱስትሪዎች በኃይል፣ በፋይናንስ፣ በሎጂስቲክስ ችግሮቻቸው ቢፈታላቸው በምርታማነታቸው የበለጠ ለውጥ እንደሚመጣ ገልጸው፤ የአጎዋ ከቀረጥ ነጻ ንግድ እንኳን ቀርቶ ኤክስፖርት አፈጻጸም ዕድገት ማስመዝገቡና በገቢ ምርቶች መተካት ላይም ሰፊ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው አትክልትና ፍራፍሬ ምርት  82 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በኢንዱስትሪ፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ ልማት፣ በአየር መንገድ እና ሌሎችም አስደናቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።