አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአገር -አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 150 ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

2

አዲስ አበበ፤ ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአገር-አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 150 ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ አገራዊ ለውጡን ተከትሉ ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እጅጉን መፈተኗን አንስተዋል፡፡

ነገር ግን መንግስት እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እውን ማድረግ መቻን ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ ለውጥ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት ተጠቃሽ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ባለፉት አራት ዓመታት 2 ሺህ 150 ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ነው ያሉት፡፡

በነባር ትምህርት ቤቶች ላይም ከ15 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በተጨማሪም መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ መቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች ከህጻንነታቸው ጀምሮ እየተመራመሩ እንዲያድጉም በኢትዮጵያ ግዙፍ የሳይንስ ሙዚየም በመገንባት ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡