የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞችን በማፍላት የአረንጓዴ አሻራ ልማቱን ለማጠናከር እየሰራሁ ነው- ኮሌጁ

234

ሀዋሳ፣ ሰኔ 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞችን በማፍላት የአረንጓዴ አሻራ ልማቱን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሳሙኤል በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በግቢው ውስጥ የሚከናወነው የደን ጥበቃና ልማት ስራ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

ኮሌጁ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገር ደረጃ እየተከናወነ ላለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ግብዓት የሚሆኑ ከሶስት ሚሊየን በላይ ችግኞችን በማፍላት ለተቋማትና ለአካባቢው አርሶአደሮች ማሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም  ሀገር በቀልና ለአከባቢው ምህዳር ተስማሚ የሆኑና ለምርታማነትን መጨመር አስተዋጽኦ ያላቸው ችግኞችን ማዘጋጀቱን አመላክተዋል ፡፡

ኮሌጁ እንደሃገር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንዲሳካ ችግኝ ከማፍላት በተጨማሪ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ሀገራዊ ሃላፊነቱ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

የኮሌጁ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መሰለ ነጋሽ በበኩላቸው በኮሌጁ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የዘርፉን ምሁራን ከማፍራት ባሻገር ባለፉት ሶስት ዓመታት  ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ማህበረሰብ በነጻ በማከፋፈል በአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ላይ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ልማቱን የሚያጠናክሩ ችግኞች ማፍላት አርሶአደሩ እንዲተክል በማድረግና

 ከመተከሉ በፊትና በኋላም ሳይንሳዊ ሂደቱን እንዲጠብቅ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ በዘመቻ መልክ የሚከናወነው የተከላ መርሃ ግብር ዘላቂነት እንዲኖረውና የተተከሉ ችግኞች በቂ እንክብካቤ እንዲያገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  የማህበረሰቡን 

ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸው ብለዋል፡፡

ኮሌጁ በሚያከናውነው የማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት ችግኞችን በየጊዜው እንደሚያፈሉ የተናገሩት ደግሞ የኮሌጁ የሃብት ማመንጫ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አሰፋ ሙሴ ናቸው።

ችግኞቹ የሚዘጋጁት የዘርፉ ምሁራን አካባያዊ ጥናት አድርገው ተስማሚነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ በመሆኑ የጽድቀት መጠናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

በሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ጴጥሮስ ቦራ በዘርፉ ባለሙያዎች 

በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው የግንዛቤ ስልጠና የተጎዳ መሬታቸው ማገገሙን ገልጸዋል፡፡

መሬት ታክሞ መዳን እንደሚችል አረጋግጠናል ያሉት አርሶአደሩ ባለፉት ሶስት 

ዓመታት በአካባቢያቸው በተሰራ ስራ ለውጥ መምጣቱን በመግለጽ ጭምር ነው፡፡

ከተመሰረተ 43 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የሚነገርለት የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ በዘርፉ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ምሁራንን እያፈራ ያለ ትልቅ ተቋም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም