በአዲስ አበባ ለደንብ ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ሕገ-ወጥ ተግባራትን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው

96

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ለደንብ ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ሕገ-ወጥ ተግባራትን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ለደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች በተቋሙ አዲስ መዋቅር ላይ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

ባለሥልጣኑ የደንብ ጥሰቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለደንብ ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየትና የቁጥጥር ሥራውን በማጠናከር ሕገ-ወጥ ተግባራትን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የደንብ ጥሰቶችን አስቀድሞ የመከላከሉን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ፉፋ ዘንድሮው አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ ደንብ የማስከበሩን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡

ይህም ሕገ-ወጥ ተግባራትን አስቀድሞ ከመከላከል ባሻገር የደንብ ጥሰቶች ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ አስችሏል ነው ያሉት፡፡

በሥልጠናው የተሳተፉ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች በበኩላቸው በቀጣይ ከሕብረተሰቡ ጋር በመተባበር የደንብ ጥሰቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም