የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ የስነ-ልቦና ጦርነትን ጨምሮ በአገር ህልውና ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን ለመመከት ትኩረት ሰጥቷል

165

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ የስነ-ልቦና ጦርነትን ጨምሮ በአገር ህልውና ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን ለመመከት ትኩረት መስጠቱ ተጠቆመ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ ሕጉ ላይ የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ አካሂዷል።

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሕግ ዳይሬክተር አማረ ኢቲቻ፤ የአዋጁን አስፈላጊነትና የተካተቱ ጉዳዮችን በሚመለከት ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ የማቋቋሚያ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው አገልግሎቱ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችሉ ተጨማሪ ሥልጣንና ተግባር ለማካተት መሆኑን ገልጸዋል።

በአገር ላይ የሚቃጣ የስነ-ልቦና ጦርነትን የመመከት ሂደት በበላይነት ለመምራትና ለማስተባበር ረቂቅ አዋጁ ትኩረት መስጠቱንም ጠቅሰዋል።

የብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ለአደጋ እንዳይጋለጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመመከት ተግባርን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም እንዲሆን በማስፈለጉ በድንጋጌው ተካቷል ብለዋል።

የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችንና አደጋዎችን ምላሽ አሰጣጥና ሥርዓትን በኃላፊነት የመምራት፣ የሚመለከታቸውን አካላት የማስተባበር ኃላፊነትን የሚያስቀምጡ ድንጋጌዎችም ተካተዋል።

የአገልግሎቱ ሰራተኞች የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ወይንም በቅስቀሳ ላይ መሳተፍ እንደማይችሉም በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ተቀምጧል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ረቂቅ አዋጁ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ መካተትና መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ተጨማሪ ጉዳዮች አንስተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሰራተኞችን ከፖለቲካ ተቋማት ነጻ ማድረግ በአዋጁ መቀመጡን በበጎ በማንሳት የስነ-ልቦና ጦርነት ምንነት፣ የመረጃ አጠቃቀምና ሌሎች ላይ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፤ ተቋሙን በትምህርትና ስነ-ምግባር ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የስነ-ልቦና ጦርነት ቋሚ ትርጉም ባይኖረውም የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ አሁን ላይ ትኩረት ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑንም አብራርተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በተባባሪነት ደግሞ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች መምራቱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም