አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የወጡ ሕጎች አፈጻጸምን የሚያመላክት አገር አቀፍ ጥናት እየተካሄደ ነው

98

ሰኔ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የወጡ ሕጎች አፈጻጸም ምን እንደሚመስል የሚያመላክት አገር አቀፍ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በክልሎች በተዘጋጁ አራት ረቂቅ አዋጆች ዙሪያ ከክልል የፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የክልል አፈ-ጉባኤዎች፣ የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩም የጠበቆች አስተዳደር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እንደ ክልል ያዘጋጁትን ረቂቅ አዋጅ ይዘት በሚመለከት የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው በመድረኩ እንደገለጹት፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ሕጎች ጸድቀው ተግባራዊ ተደርገዋል።

የፀረ-ሽብር ሕግ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፣ የሚዲያ ሕግ ከለውጡ ወዲህ የወጡ ህጎች መሆናቸውን በአብነት አንስተው፤ በቀጣይም ሕግ የማውጣቱን ሂደት ፍትሃዊና አሳታፊ በማድረግ የዜጎችን መብትና ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሕጎችና አዋጆች አፈጻጸም ወጥ አለመሆኑን የሚያነሱ አካላት መኖራቸውን ገልጸው፤ ጥናትን መሰረት በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል።

በዚህም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የወጡ ሕጎች አፈጻጸም ምን እንደሚመስል የሚያመላክት አገር አቀፍ ጥናት እየተካሄደ  መሆኑን ተናግረው፤ በጥናቱ የሚለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሰሎሞን አባይ በበኩላቸው፤ በሀገር ደረጃ የሚወጡ ሕጎች  ውጤታማ እና ሕብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉት ወጥነት ባለው መልኩ በክልሎችም ተግባራዊ ሲሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የሕግ አፈጻጸም አለመኖር በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚጎዳ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም