የፈረንሳይ መንግሥት በአማራ ክልል በጦርነት ለወደሙ የጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋም የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት አደረገ

91

ሰኔ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፈረንሳይ መንግሥት በአማራ ክልል በጦርነት ለወደሙ የጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋም የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት አደረገ፡፡

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ተፈራርመዋል፡፡

የድጋፍ  ስምምነቱ በዋናነት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል መልሶ ለመገንባት የሚውል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በሂደትም ሌሎች በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማትን የመደገፉ ሥራ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ የዛሬው የድጋፍ ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የፈረንሳይ መንግሥት የጤና ተቋማትን ለማቋቋም ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ድጋፉ መንግሥት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የፈረንሳይ መንግሥት በጤናው ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ያደረገውን ድጋፍ በአብነት አንስተው፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጋሹ ክንዱ በበኩላቸው፤ ድጋፉ በተለይ የሕክምና ተቋማቱን በጤና ግብዓት ለማሟላት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም