ኢጣሊያ ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት ድጋፍ ታደርጋለች

3

ሰኔ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢጣሊያ ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት ድጋፍ የምታደርግ መሆኑን የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዊጂ ዲ ማዩ ተናገሩ።

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዊጂ ዲ ማዩ የ22 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ብድሩ ለቡልቡላ፣ ቡሬ፣ ይርጋለምና ባዕከር የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማጠናከሪያ እንዲሁም በፓርኮቹ ዙሪያ ለሚቋቋሙ የገጠር ሽግግር ማዕከላት ግንባታ የሚውል መሆኑ ታውቋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ሁለቱ አገሮች ለረጅም ዘመን የዘለቀ በሁለትዮሽ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዘርፎች ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የብድር ስምምነቱ ይበልጥ ትስስሩን የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በኮቪድ-19፣ ጦርነትና ድርቅ ፈተናዎች ቢኖሩም አገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎችን ተፈጻሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በያዘችው ምጣኔ ሃብታዊ መዋቅራዊ ሽግግር የስራ ዕድል ፈጠራ እና የአምራች ዘርፍ ማጠናከር ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።

የግብርና ምርቶችን ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ኢንቨትመንት ስበትን ማጠናከርና ለባለሀብቶች ማበረታቻዎችን ማስፋፋት ላይ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዕለቱ የተደረገው የብድር ስምምነት የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፉን መሻሻል፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለአርሶ አደሮች ገቢ መሻሻል፣ የወጪ ምርትን እምርታና ከውጭ ገቢ ምርቶችን በመተካት ረገድ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዊጂ ዲማዩ፤ የብድር ስምምነቱ ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝንተ ያረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፤ ኢኮኖሚያዊ የትብብር ስምምነቶች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አረጋገጠዋል።

የብድር ስምምነቱ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ለሚገኘው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማነት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የአምራች ዘርፉን፣ የመንግስት እና የግል ዘርፉን ትብብር እንደሚያጎለበትም አመላክተዋል።

በወቅቱ የተከሰተውን ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ቀውስ ለመቋቋም ኢጣሊያ በዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች በኩል የበኩሏን ሚና እንደምትወጣም ጠቁመዋል። 

ኢጣሊያ ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት ድጋፍ  የምታደርግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።