የሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መቸገራቸውን ገለጹ

199

ደሴ፣ ሰኔ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች በከፋ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ምክንያት ለስቃይ መዳረጋቸውን በመግለጽ ቅሬታ አሰሙ።

ግንባታው የተጓተተው የ56 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የውሃ ፕሮጀክት አስመልክቶ ለምናነሳው ጥያቄ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሐያት ሁሴን “ሐይቅ ዳር ተቀምጠን ውሃ ጠማን ማለት ቢያሳፍርም በንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እየተሰቃየን ነው” ብለዋል።

ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የውሃ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እስካሁን ባለመጠናቀቁ ከችግር መላቀቅ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

የሶስት ልጅ እናት የሆኑት ወይዘሮ ሐያት ''በችግሩ ምክንያት ልጅ አዝዬ ውሃ ፍለጋ እየተንከራተትኩ ነው። ንጽህናው ያልተረጋገጠ አንድ ጄሪካን ውሃ በ30 ብር ለመግዛት ተገድጃለሁ'' ብለዋል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ተማሪ ኢልሃም አህመድ በበኩሏ ውሃ ለማግኘት ከአንድ ሰዓት በላይ በእግር ተጉዛ እንደምታመጣና በዚህም ምክንያት ከትምህርት ቤት ለመቅረት እየተገደደች መሆኑን ገልጻለች፡፡

“በሳምንት አንድ ጊዜ ይመጣልን የነበረው ውሃ ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፤ አሁን ሀሳቤ ለትምህርቴ ሳይሆን ለውሃው ነው'' ብላለች፡፡

የውሃ ፕሮጀክቱ ሲጀመር በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል ቢባልም በመዘግየቱ የሚመለከተውን አካል ብንጠይቅም ነገ ዛሬ ከማለት ውጭ መፍትሔ አላገኘንም ያሉት ደግሞ አቶ ይማም አብዱራህማን ናቸው።

ማህበረሰቡ የተጀመረው ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ የጉልበትና የገንዘቡ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል። 

ይሁን እንጂ በየደረጃው ያለው አመራር ውጤታማ ስራ መስራት ባለመቻላቸው ከውሃ ችግሩ ሊላቀቁ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ውሃና ኢነርጅ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ጽጌ በበኩላቸው የሐይቅ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግር አስከፊ መሆኑን በመረዳት ፕሮጀክቱ በ56 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ በ2011 ዓ.ም መጀመሩን ያስታውሳሉ።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ ቢጠናቀቅም ፕሮጀክቱ ውሃው ከሚመጣበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር ውዝግብ በመፈጠሩ በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም፤ ይህም ሕዝቡን አስከፍቷል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ ወጪ በማውጣት ዲዛይን ተሰርቶ በ35 ሚሊዮን ብር በአንድ ዓመት ውስጥ ውሃ እንዲገባ ከግንባታው ተቋራጭ ጋር ውል መፈረሙን ገልጸዋል።

ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት በአሁኑ ወቅት መሰረታዊ ችግሮችን መቅረፍ በመቻሉ ውሃውን ከመስመሩ ጋር ማገናኘት ብቻ መቅረቱን ገልጸው፤ “ፕሮጀክቱ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም