ከኦሮሞ ህዝብ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህልና ወግ የአሁኑ ትውልድ ብዙ ሊማር ይገባል – ከንቲባው

2

ጭሮ ሰኔ 6/2014(አዜአ)–ዘመናዊ የህዝብ አስተዳደር ስርዓት ባልነበረበት ከትናንቱ የኦሮሞ ህዝብ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህልና ወግ የአሁኑ ትውልድ ብዙ ሊማር ይገባል ሲሉ የጭሮ ከተማ ከንቲባ አቶ መሐመድ ኡመር ገለጹ።

የኦሮሞ ህዝብ እርስ በርስ የሚረዳዳበትና አንዱ ለአንዱ ደራሽነቱን የሚያሳይበት የመረዳጃ ስርዓት ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የንቅናቄ መድረክ ትናንት በጭሮ ከተማ ተካሄዷል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ ኡመር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት “ቡሳ ጎኖፋ” ሁሉም ካለው ላይ እንዳቅሙ የተቸገረን መደገፍና መርዳት የሚችልበት ባህላዊ ስርዓት ነው”፡፡

ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲገጥሙ የተቸገረን ለመታደግ ከጎኑ ለመቆምና የችግር ቀኑን እንዲሻገር ወገን ደጋፊነቱን የሚያሳይበትና ከባህላዊው የገዳ ስርዓት የተቀዳ እንደሆነም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

በጥንት ዘመን ዘመናዊ የህዝብ አስተዳደር ስርዓት ባልነበረበትና የኦሮሞ ህዝብ እርስ በርስ የሚረዳዳበት የመረዳጃ ስርዓት እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

የቀድሞ እናቶችና አባቶች በችግር ጊዜ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህልና ወግ የአሁኑ ትውልድ ብዙ ሊማርበት የሚገባው መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

ለተግባራዊነቱም እድሜው ከ9 ዓመት በላይ የሆነ ሁሉም  የአካባቢው ነዋሪ “ቡሳ ጎኖፋ” በመደገፍና የአቅሙን ድጋፍ እንዲያደርግ ከንቲባው በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ ጠይቀዋል፡፡

የ”ቡሳ ጎኖፋ” ንቅናቄ ተሳታፊ ወይዘሮ ዘሀራ ኢብራሂም በበኩላቸው በድርቅና በጦርነት ሳቢያ ያጋጠመውን መፈናቀል፣ የጤና መስተጓጓልና ረሃብ ለመታደግ የጋራ ጉልበት የሆነውን ቡሳ ጎኖፋን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ጫልቱ አብዱልአብ በሰጡት አስተያየት ዛሬ የተቸገረን መርዳት ለነገ የሚተርፍ ዜጋ መፍጠር በመሆኑ ህዝቡ ባለው አቅም ወገኑን የመደገፍ ግዴታውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

እርሳቸውም የአቅማቸውን ያህል ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ቡሳ ጎኖፋ” በጨፌ ኦሮሚያ በአዋጅ የጸደቀና በቅርቡም በክልሉ መንግስት የንቅናቄ ዘመቻ እየተካሄደበት ያለ ባህላዊ የመረዳጃ ስርዓት ነው።