ሸካ ዞን በአንድ ጀንበር 2 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተተከለ

152

ሚዛን አማን ሰኔ 06/2014 (ኢዜአ) ... በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን በአንድ ጀንበር 2 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተተከለ።

የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከቡና የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማስፋት የቡና ምርትና ምርታማነት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  መግለጹም ተመላክቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ በተከላ መርሃግብሩ ላይ እንዳሉት የቡና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል።

አካባቢው ቡና በስፋት የሚመረትበት ቢሆንም ከምርቱ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በማግኘቱ ረገድ ግን ብዙ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።

ከቡና የሚገኘው ዘርፈ ብዙ  ጥቅም የአርሶ አደሩንና የሀገርን ኢኮኖሚ ከፍ እንዲያደርግ ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ በተከላና ለቀማ ወቅት በከፍተኛ የጥራት ደረጃ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልሉ ከ541 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ማሳ የሚገኝ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት እስካሁን ከ61ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡንም አስታውቀዋል አቶ አስራት።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በዞኑ ያለውን ከ83 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የቡና ማሳ ከፍ ለማድረግ በክረምት ወራት የሚተከል ከ7 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ማዘጋጀታቸውን አመላክተዋል።

ከዚህም በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች 2 ሚሊዮን የተሻለ ምርት ይሰጣል ተብሎ የተዘጋጀን ችግኝ በዛሬው የቡና ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተተክሏል ብለዋል።

ዞኑ በ2014 በጀት ዓመት እስከ ግንቦት ወር ድረስ 17 ሺህ 3 መቶ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን አስታውሰው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ7ሺህ 3 መቶ ቶን ቡና ብልጫ አለው ብለዋል።

የየኪ ወረዳ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ ካሣ ወረዳው በስፋት ቡና አምራች እንደሆነ ገልጸው የማሳ ሽፋን ከመጨመር ጎን ለጎን ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል በአዲስ የመተካት ሥራም በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየኪ ወረዳ ዝንኪ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሞዴል አርሶ አደር አስማማው ታደሰ በበኩላቸው የቡና ችግኝ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ማዘጋጀት መጀመራቸውን ጠቅሰው ለራሳቸው ከሚተክሉት ባለፈ ለሌሎች ሽጠው እየተጠቀሙ መሆናቸውን አክለዋል።

የቡና ችግኝን ለአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች እያከፋፈሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ለየአካባቢው የአየር ሁኔታ የሚመች የቡና ዝርያን በባለሙያ አረጋገጠው እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል።

በዘንድሮ አመት 90 ሺህ የቡና ችግኝ ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ አስማማው፤ በቀጣይ ዓመት መጠኑን ከፍ አድርገው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም