የአፋርና የሱማሌ ኢሳ ማህበረሰብ በደም የተዋሃደ አንድ ህዝብ ነው - የሰላም ሚኒስቴር

102

አዳማ ሰኔ 06/2014/ ኢዜአ/... በሃይማኖት፣ በባህልና በደም የተጋመደው የአፋርና የሱማሌ ኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊውን የግጭት አፈታት ዘዴን ተግባራዊ በማድረግ በመካከላቸው ዘላቂ ሰላም መፍጠር ይቻላቸዋል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

የአፋርና የሱማሌ ኢሳ ማህበረሰብ መካከል አልፎ አልፎ የሚፈጠሩትን አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱ ጎሳዎች የሃይማኖት መሪዎችና ዑጋዞችን ያካተተ 10 አባላት ያለው ኮሚቴ ተዋቅሯል።

ኮሚቴው ሁለቱን ማህበረሰብ ቀርቦ በማናገርና የግጭቶቹን መንስዔዎች በማጥናት በመካከላቸው ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ታስቦ የተቋቋመ መሆኑም ተመላክቷል።

ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት  በሁለቱ ማህበረሰብ መካከል በግጦሽና በውሃ ምክንያት አልፎ አልፎ ግጭቶች የሚፈጠሩ ቢሆንም ሁለቱ ህዝቦች በባህላዊ መንገድ ግጭቶችን በመፍታትና በአብሮነት ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

በተለይ በሁለቱ ህዝቦች መካከል "በባህል፣ በሃይማኖትና በደም የተጋመደ ማንነት አለ" ያሉት ሚኒስትሩ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ደግሞ በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንግዳ ነገር አይሆንባቸውም ነው ያሉት።

"እጃችን ላይ የምንኮራባቸው ባህላዊ እምቅ የግጭት አፈታት አቅም አለ" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "አሁንም ሰላማችንን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በባህላችን ማዕቀፍ መስራት ይገባል" ብለዋል።

"ከግጭቶቹ በስተጀርባ የተለያዩ የፖለቲካና የጥቅም ፍላጎት ቢኖርም ችግሮቹን በራሳችን የመፍታት ባህልና እሴት እንዳለን ግን ላፍታም መዘንጋት የለብንም ሲሉ አሳስበዋል።

በዚህም ከሁለቱ ክልሎች አጎራባች ቀበሌዎችና ወረዳዎች ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ማህበረሰብ አቀፍ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ የተፈጠረው ወቅታዊ ችግርም የሰላሙ ባለቤት ከሆነው ህዝብ በላይ እንደማይሆን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሁለቱ ክልል መንግስታት ህዝቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ግጭቶቹን መፍታት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

በዚህ ውይይት በሁለቱ ማህበረሰብ መካከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችሉ የጋራ ስምምነትና የመቋጫ ሃሳቦች ላይ እንደተደረሰበትም ጠቅሰዋል።

የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እንዳሉት ግጭት እንዲቆም የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለማስፈፀም፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት ይሰራል።

የፖለቲካ አመራሮች ፍትሃዊ የመፍትሔ አካል በመሆን የአካባቢውን ወገኖች ደህንነትና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

"ያለፉ ቁስሎችን በመነካካት መፍትሔ አናመጣም" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ "የሁለቱ ክልል የፖለቲካ አመራር ግጭቱን ለማስቆምና በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሙሉ አቅማችን እንሰራለን" ነው ያሉት።

"ቁልፉ ነገር ሁለታችን በመድረኩ ዓላማ ላይ በመግባባት የችግሮቹ የመፍትሔ አካል መሆናችን ነው" ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አወል አርባ ናቸው።

ግጭቶች በየትኛውም ቦታና አካባቢ ሊፈጠሩ ይችላሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ "ግጭቶች ወደ ቀውስ እንዳያመሩ ግን ራሳችን የመፍትሔው ባለቤት በመሆን ሰላም ማረጋገጥ አለብን" ብለዋል ።

በግጭት ማንም ተጠቃሚ አይደለም ያሉት አቶ አወል፤ "ችግሮቻችንን ለመፍታት ያለንን ባህልና ልምድ በመጠቀም የጋራ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በትብብርና በቅንጅት መስራት አለብን" ነው ያሉት ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም