ጣልያን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን ትደግፋለች --የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

122

ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/ ጣልያን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊውጂ ዲ ማዮ ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊውጂ ዲ ማዮን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱን ተከትሎም ሁለቱ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት ሁለቱ አገራት ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በውይይታቸው በዋናነት በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራትን የጋራ ጥቅም ባማከለ መልኩ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር  መስማማታቸውንም እንዲሁ።

የጣልያን መንግሥት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያራምደውን ሚዛናዊ አቋምም አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ሥራ የጣልያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማድነቃቸውንም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊውጂ ዲ ማዮ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ጣልያን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምትደግፍም ነው የገለጹት፡፡

ጣልያን ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት እንደምትሰራም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የወሰዳቸው እርምጃዎች የሚደነቁ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ እያደረገ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያና ጣልያን በኢኮኖሚ፣ፖለቲካና ባህላዊ መስኮች ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም