የትራፊክ ሕግ ማሻሻያ ሊደረግበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትራፊክ ሕግ ማሻሻያ ሊደረግበት ነው

ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የትራፊክ ሕግ ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑን የመንገድ ደኅንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አዲሱን የትራፊክ ሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማስመልከት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት አድርገዋል።
የትራፊክ ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ በመከላከል ለመቀነስ መሆኑ ተገልጿል።
የአገልግሎቱ የመድህን ፈንድ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አዲል አብዱላሂ፤ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል ለረዥም ዓመታት ያገለገለውን የትራፊክ ሕግ ማሻሻል አንዱ መፍትሔ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሀገሪቱ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ሥራ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲሱ የሕግ ማዕቀፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ማኅበረሰቡ እንዲወያዩበት በማድረግ የግብአት ማሰባሰብ ሥራ ማከናወኑ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረት የዛሬው የውይይት መድረክ መዘጋጀቱንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በመድረኩ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በተደረገው ውይይት የሕግ ማሻሻያው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተብራርቷል።
ለትራፊክ አደጋ ዋነኛው መንስኤ ፍጥነት መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስና ቸልተኝነትም ሌላኛው ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።
በመሆኑም አሁን የተሻሻለው ሕግ እነዚህንና ሌሎች የትራፊክ አደጋ መንስኤዎችን ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።