ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም አሸባሪውን ሕወሓት በመደገፍ በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ይቅር የማይባል በደል እየፈጸሙ ነው

116

ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም የትግራይ ክልል ሕዝብን ለከፍተኛ ችግርና እንግልት እየዳረገ ያለውን የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በመደገፍ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል እየፈጸሙ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ገለጸ።

አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸም ጀምሮ አገር ለማፍረስ የተለያዩ የጥፋት ተግባራትን እየፈጸመ መሆኑ ይታወቃል።

ለሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ የሚገባውን ድጋፍ ሁሉ ለራሱ ጥቅም በማዋል ሕዝቡን ለከፋ ችግር እየዳረገ ስለመሆኑም በርካቶች እየተናገሩ ይገኛሉ።

በክልሉ ዜጎች ልጆቻቸውን በግዳጅ ለጦርነት እንዲያሰልፉ በማድረግና የተለያዩ በደሎችን በመፈጸም ግንባር ላይ መጠመዱ እየታወቀ አንዳንዶች የአሸባሪውን ተግባር ደግፈው ቆመዋል።

የአሸባሪውን ቡድን እኩይ ዓላማ ከደገፉት መካከል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም፤ በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ይቅር የማይባል በደል እየፈጸሙ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ገልጿል።

የትዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሐጎስ ግደይ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ግለሰቡ ቀደም ሲልም የሕወሓት አባል መሆናቸውን አስታውሰው፤ አሸባሪውን ደግፈው በሕዝብ ላይ በደል በመፈጸም ተባባሪ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አሁን የሚደግፉት አሸባሪ ቡድን የትግራይ ክልል ሕዝብ ሰቆቃና መከራ እንዲራዘም እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፋቸው ቆይቶ ሊጸፅታቸው ይችላል ብለዋል።

የትዴፓ ምክትል ሊቀመንበር መስፍን ደሳለኝ፤ ግለሰቡ እንዲህ አይነት ትልቅ ሥፍራ ላይ ተቀምጠው በጎ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ሲችሉ አሸባሪን ደግፈው መቆማቸው አሳፋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ሕወሓት በሥልጣን ላይ በቆየባቸው 40 ዓመታት ለትግራይ ሕዝብ የጠቀመው አንዳችም ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።

መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ወደ ትግራይ ክልል ስብዓዊ ድጋፍ ያለገደብ እንዲገባ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምሮ ሰብዓዊ ድጋፍን ለራሱ ጥቅም በማዋል የሚታወቀው አሸባሪው ሕወሓት አሁንም በዘረፋው ሕዝብን ለችግር መዳረጉን ቀጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም