በክረምት ወቅት ሕብረተሰቡን ለጉዳት የሚዳርጉ የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች መፍትሔ ይሻሉ--የመዲናዋ ነዋሪዎች

105

ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/በክረምት ወቅት ሕብረተሰቡን ለጉዳት የሚዳርጉ የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች መፍትሔ እንዲበጅላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የአደጋ ስጋት ምንጭ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎችን የመቀየር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡

በክረምት ወቅት ሕብረተሰቡን ለጉዳት ከሚዳርጉ አደጋዎች መካከል አንዱ በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ምክንያት የሚከሰት አደጋ ተጠቃሽ ነው፡፡

በተለይ በክረምት ዝናብ ምክንያት የሚወድቁ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች አደጋ ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ ያረጁና በመኖሪያ ቤት የሚገኙ  የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በተለይ በክረምት  ወቅት አደጋ እንዳይፈጥሩ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቀዋል፡፡

እነዚህ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በዝናብ ምክንያት  የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት እያደረጉ ስለመሆኑም ነው ያነሱት፡፡

ምሰሶዎቹ በዘንድሮው ክረምትም ለአደጋ ሊያጋልጡን ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በለጠ ታፈሰ የተባሉ አስተያየት ሰጪእንዳሉት ምሰሶዎቹ በየቤቱ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረው ኮሚቴ አቋቁመን አመልክተናል መልስ ልናገኝ ግን አልቻልንም ብለዋል።

አቶ በቀለ ኡርጌ በበኩላቸው የተጠላለፉ መስመሮች ወጥነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቅሰውያዘመሙ ፖሎች ቀጥ ሊሉ ይገባል  ወይም መለወጥ አለባቸው ።

ከአሁን በፊት ፖል እንደሚቀየር ቢነገረንም አልመጡም ያሉት አቶ በቀለ፣ " ተመላልሰን ኮሚቴ አዋቅረን ጠይቀናል " ብለዋል፡፡ በተለይም ለህፃናቶች ስጋት እንዳደረባቸው ነው የተናገሩት፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ "ህብረተሰቡ ለአደጋ ከሚጋለጥ፣ በመብራት እጦትና መብራት ከሚያመጣው አደጋ ከመከሰቱ በፊት መብራት ኃይል አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድልን በአካባቢው ህዝብ ስም ጥሪ እናደርጋለን።"ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ በቀለ ክፍሌ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ማደግን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በዚህም በሕብረተሰቡ ላይ አደጋ የመፍጠር ስጋት የሚያሳድሩ መስመሮችና ምሰሶዎችን የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማሻሻያና የጥገና ሥራውም በመዲናዋ በሚገኙ 30 ማዕከላት እንዲሁም ዲስትሪክቶች እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ።

ለአብነትም "ፓወር ቻይና" በተሰኘ ድርጅት አማካኝነት በመዲናዋና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች 625 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ማሻሻያ ሥራ መስራቱን ጠቅሰው፤ የማሻሻያ ሥራዎችም ለውጥ እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በክረምት ወቅት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የቅድመ-ጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  ገልጸው፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ቢቋረጥም በፍጥነት ለመጠገን ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።  

ክረምት እየመጣ መሆኑን ተከትሎ የቅድመ-መከላከል ጥገና ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር  መላኩ ታዬ ናቸው።

አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ በተመረጡ ከተሞች የኔትወርክ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንና በዚህም የኃይል መቆራረጥን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም