በበጀት ዓመቱ በህልውና ዘመቻውና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ አመርቂ ስራ ተሰርቷል - የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል

87

ሀዋሳ ሰኔ 6/2014 (ኢዜአ).... እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት በህልውና ዘመቻው እና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ በክልሉ አመርቂ ስራ መከናወኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የ2014 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈፃፀምን በሀዋሳ ከተማ  እየገመገመ ነው።

በግምገማ መድረኩ  ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የክልሉ መንግስት ትኩረት አድርጎ ከሰራባቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሀገር ሉአላዊነት በማስከበር ዘመቻውና የክልሉን ዜጎች ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ ዋነኞቹ ናቸው።

በእነዚህም መላው የክልሉን ህዝብና የአመራር አካላትን በማነቃነቅ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤቶች  መመዝገቡን አመላክተዋል።

በተለይ በህልውና ዘመቻው ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በርካታ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል ተሳትፈዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትም በተመደቡበት የግዳጅ ቀጠና ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ሆነው ግዳጃቸውን በአኩሪ ገድል መፈፀማቸውን ነው የተናገሩት።

መላው የክልሉ ህዝብም በሞራል፣ በስንቅ ዝግጅትና በፋይናንስ በመደገፍ የማይተካ ሚናውን በላቀ ደረጃ  መወጣቱን በማስታወስ ለዚህም መላው ህዝቡ ሊመሰገን እንደሚገባ ነው ያወሱት።

በዘመቻውም ኢትዮጵያን  በኃይል ለማንበርከክ የሚሹ ጠላቶቿ መቼም እንደማይሳካላቸው ያመላከተ ድል የተገኘበት መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የክልሉን ዜጎች ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድም በተለይ የሽብር ተልዕኮ ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ከህዝብ ጋር ሆኖ በመታገል እኩይ ዓላማቸውን ማምከን መቻሉን ነው ያብራሩት።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ ላይ የክልሉ መንግስት የ2014 በጀት ዓመት በጥልቀት ከተገመገመ በኋላ የ2015 በጀት ዓመት ዋና ዋና ተግባራት ላይም ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በግምገማ መድረኩ ላይ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣ የተጠሪ ተቋማትና የዘርፍ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም