የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የገንዘብ ሽልማት አበረከተ

121

ሰኔ 5/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በዩጋንዳ በተከናወነው የሴቶች የሴካፋ ውድድር 3ተኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የ5 ሚሊዮን ብር ሽልማት አበረከተ።

በአንደኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድር ለተሳተፈው የአዲስ አበባ የስፖርት ልዑካን ቡድንም የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሽልማቱ ወቅት "ውጤት ያመጡ ስፖርተኞችን ማበረታታት ለተተኪዎቻቸው ጭምር ብርታት የሚሰጥ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።

ከዚህ አኳያ ሉሲዎቹ ያመጡት ውጤት ሴቶች ጠንክረው ከሰሩ  ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ፣ ብርታትና ብቃትም እንዳለቸው ያመላክታል ብለዋል።

በተጨማሪም  በአንደኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች  ኦሊምፒክ ውድድር ለተሳተፈው የአዲስ አበባ የስፖርት ልዑካን ቡድን የ5 ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክቷል።

የአዲስ አበባ የስፖርት ልዑካን ቡድን በአንደኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ  ውድድር በ46 ወርቅ ፣ በ30 ብር ፣ እና በ34 ነሐስ በአጠቃላይ በ110 ሜዳሊያዎች 1ኛ በመውጣት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በመሆኑም ቢሮው በ12 የኦሊምፒክ ስፖርቶችና ከኦሊምፒክ ውጪ በሆኑት የቼዝና ኢንትርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት ተወዳድረው ላሸነፉ የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ልዑካን ቡድን አባላት የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡

በዚህም የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡት ለእያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡት የ7 ሺህ ብር እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡት የ5 ሺህ ብር ሽልማት ተሰቷቸዋል።

በውድድሩ ብስክሌት ውድድር ከተዘጋጁት 6 ሜዳሊያዎች 6ቱም የተገኘበትና በአትሌቲክስ ውድድር ከተዘጋጁት 32 ሜዳሊያዎች 20 ሜዳሊያዎች የተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ ልዑካን ቡድን አባላት መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም