በኮርፖሬሽኑ የተሞከረውን ስኬታማ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ተሞክሮ ለማስፋት እንሰራለን- የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች

3

ሰኔ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሞከረውን ስኬታማ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ተሞክሮ ለማስፋት እንደሚሰሩ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት እና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች ትናንት የተመረቀውን የገርጂ መኖሪያ መንደርን ጎበኝተዋል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝቱን ያካሄዱት የፓርቲውን ያለፉት አሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት  ግምገማ መድረክ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ መሆኑም ታውቋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ፓርቲው የሕዝቦችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው።

ከእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች አንዱ የመኖሪያ ቤት ግንባታ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም መንግሥት የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በተለመደው መልኩ የቤት አቅርቦት ችግር መቅረፍ እንደማይቻል በማሰብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ያከናወነው ግንባታ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ይህንኑ ተሞክሮ በማጠናከር የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በፓርቲው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማሕበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ፤ ወደፊት የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚቻል ማሳያ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያከናወነው የመኖሪያ መንደር ግንባታ ጥራቱ የተሻለ፣ ዋጋውም ተመጣጣኝና በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ለቀጣይ ስራ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የከተሞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ የታየበት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት ነብዩ ስሁልሚካኤል፤ የገርጂ መኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት ለሌሎች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አብነት የሚሆን ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የፓርቲው አማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ እና የፓርቲው የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም ማርሻሎ ይህንኑ ተሞክሮ ወደ አካባቢያቸው ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ከዚህ በኋላ በመደበኛ አካሄድ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ አዲስ እይታና አዲስ ምልከታ የተካተተበት ሥራ መሥራት ግዴታ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በበኩላቸው፤ የገርጂ የመኖሪያ መንደር ግንባታን አገር ውስጥ ባልተሞከረ ቴክኖሎጂ ማከናወን መቻሉን ጠቅሰው፤ ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ጠንካራ የፕሮጀክት አፈጻጸም ሥራ የመኖሪያ መንደሩን በአጭር ጊዜ እውን ማድረግ መቻሉን አክለዋል።

ቴክኖሎጂው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መተማመን መፍጠር አስፈላጊ እንደነበር አስታውሰው፤ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ረገድ የተሳካ ስራ ማከናወኑን አብራርተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ብቻ 16 ሕንጻዎችን የገነባ ሲሆን፤ 510 ቤቶችን በአንድ ዓመት ተኩል አጠናቋል።